አፄዎቹ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ስምምነት ፈፅመዋል

ፋሲል ከነማ ከከፍተኛ ሊጉ ሁለት አዳዲስ ፈራሚዎችን አግኝቷል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2016 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ አመቱን ያሳለፈው ፋሲል ከነማ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ቡድኑን የሚለቁ ተጫዋቾች በመኖራቸው እነርሱን በመተካት ቡድኑን ለማጠናከር በረከት ግዛው እና አሚር ሙደሲርን ቀደም ብለው ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት አዳዲስ ፈራሚዎችን ከከፍተኛ ሊግ ለማስፈረም ስምምነት መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቢኒያም ላንቃሞ የቡድኑ አዲሱ ተጫዋች ነው። ከሲዳማ ቡና የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው በአጥቂ እና አማካይ ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ቁመታሙ ተጫዋች በመቻል እና ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደግሞ በወልዲያ መለያ ያሳለፈ ሲሆን በተለይ በተጠናቀቀው ዓመት ከቡድኑ ጋር ጥሩ ጊዜን ከማሳለፉ በተጨማሪ ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥሮ ለቀጣዩ ዓመት ደግሞ መዳረሻው የአፄዎቹ ቤት በሁለት ዓመት ሆኗል።

ሌላኛው ፈራሚ ወጣቱ አማካይ ኃይሌ ዘመድኩን ነው። ከአፋሯ አዋሽ የተገኘው እና ምንም እንኳን አማካይ ላይ ይጫወት እንጂ ሁለገብ ሚና ያለው ይህ ተጫዋች ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ከአንደኛ ሊጉ እስከ ተጠናቀቀው ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታን ያደረገ ሲሆን በሀዋሳ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በተደረጉበት ወቅት ተጫዋቹን የተመለከቱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀጣይ የቡድናቸው ፈራሚያቸው አድርገውታል።