ኢትዮ ኤሌክትሪክ የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል

ወደ ዝውውሩ የገባው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአራት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ማራዘሙ ታውቋል።

ለከርሞ ወደ ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ታሪካዊው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ዝውውሩ በመግባት ግብጠባቂ አሸብር ተስፋዬን፣ አብዱላዚዝ አማን፣ ገለታ ኃይሌ፣ ሄኖክ ገብረህይወት፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና ዲንግ ኪያርን ለሁለት ዓመት ማስፈረሙ ይታወቃል። አሁን ደግሞ ቡድኑ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲመለስ ያስቻሉትን የአራት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ለሁለት ዓመት ማራዘሙ ታውቋል።

ጌቱ ባፋ ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ሲሆን ከዚህ ቀደም በነቀምት ከተማ ሲጫወት ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በምክትል አምበልነት እየመራ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጎ የነበረው ተጫዋቹ ዘንድሮም በተመሳሳይ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሎ ክለቡን በተከላካይነት እና በአምበልነትም ጭምር ወደ ሊጉ ያሳደገ የኋላ ደጀን የቡድኑ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመባል መሸለሙ ይታወቃል።

ያሬድ የማነ ሌላው ለመቆየት ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ሲሆን የግራ መስመር ተከላካዩ ያሬድ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያገለገለ በቡድኑ መውጣትም መውረድም አብሮ የነበረ ወደ ፊትም ተስፋ የሚጣልበት ወጣት ተጫዋች ሲሆን ክለቡም የዓመቱ ወጣት ተሸለሚ አድርጎት ነበር።

ከድሬደዋ ተስፋ ቡድን ተገኝቶ በፕሪሚየር ሊጉ ሲጫወት የተመለከትናው ወጣቱ አማካይ ሚኪያስ ከሳሁን ዘንድሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል ቡድኑ ወደ ሊጉ እንዲመለስ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል ነው።

ውሉን ያራዘመው አራተኛ ተጫዋች ባለ ብዙ ልምዱ እንዳለ ዘውገ ነው። በአዳማ ከተማ፣ ወልዋሎ፣ በሰበታ ከተማ እና በሌሎችም ክለቦች የተጫወተው እና ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወደ ሊጉ ካሳደገ በኋላ ዘንድሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደግ ቁልፍ ሚና ተወጥቷል።