መቐለ 70 እንደርታዎች የሁለት ተጫዋቾች ዝውውር አገባደዱ

ምዓም አናብስት ስብስባቸውን በማጠናከሩ ቀጥለዋል።

አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬን በመንበሩ የሾሙት መቐለ 70 እንደርታዎች በቀጣዩ ዓመት ለሚሳተፉበት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ጠንክረው ለመቅረብ እንዲረዳቸው በትግራይ ዋንጫ ተሳታፊ በነበረው ቡድን ውስጥ የነበሩ ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት በማራዘም አዳዲስ ደግሞ ሠለሞን ሀብቴ ፣ ቦና ዓሊ ፣ ሸሪፍ መሐመድ ፣ ያሬድ ከበደ ፣ ሶፎኒያስ ሰይፈ ፣ ያሬድ ብርሀኑ ስብሰባቸው የቀላቀሉ ሲሆን አሁን ደግሞ መናፍ ዐሊና ተመስገን በጅሮንድን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

ከአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን ተገኝቶ እናት ክለቡን አራት የውድድር ዓመታት በማገልገል ወደ ባህርዳር ከተማ አቅንቶ በጣና ሞገዶቹ ሁለት የውድድር ዓመታት ያሳለፈው ይህ ተከላካይ ያለፉት ሁለት ዓመታት በፋሲል ከነማ ሲጫወት ቆይቷል። ሌላው ቡድኑን የተቀላቀለው የቀድሞው የሺንሺቾ ከተማ ፣ ደደቢት ፣ ኢኮስኮ እና ሲዳማ ቡና ተጫዋች የነበረው ተመስገን ላለፉት ሦስት ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ቆይታን ካደረገ በኋላ በዛሬው ዕለት በአንድ ዓመት የውል ዕድሜ ወደ መቐለ አምርቷል።