ፈረሰኞቹ በቀድሞው የታዳጊ ቡድን ተጫዋቻቸው በመጀመር ወደ ዝውውር ገብያው ገብተዋል።
በሊጉ ደማቅ ታሪክ ካላቸው ክለቦች ቀዳሚ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2017 የውድድር ዘመን የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ከተከፈተ ወዲህ ወደ ስብስባቸው አዳዲስ ተጫዋቾችን ሳይቀላቅሉ ቆይተዋል። በአመዛኙ የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾችን ውል በማራዘም ማቆየት ያልቻሉት ፈረሰኞቹ ለሳምንታት ቡድኑን ለቀጣይ ዓመት ለማጠናከር በማሰብ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቆይተው አሁን የመጀመርያ ፈራሚያቸውን ለማግኝት ተስማምተዋል።
ፈረሰኞቹን የተስማማው የመጀመርያው ተጫዋች የመስመር አጥቂው በፍፁም ጥላሁን ነው። ክለብ ደረጃ የእግርኳስ ህይወቱ መነሻ ያደረገው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ከ17 ዓመት በታች ቡድን ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ከተጫወተ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በማምራት ሁለት ዓመታትን በማሳለፍ ወደ ጣና ሞገዶቹ በመሄድ የሁለት ዓመት ቆይታ አድርጎ እንደነበረ ይታወቃል። አሁን ዳግም ከዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊው ቤት በመመለስ ለሁለት ዓመት ለመጫወት ተስማምቷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እያደረጉት ካለው ጥረት ባሻገር የቡድኑን ቀጣይ አሰልጣኝ ለመሾም ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።