ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በይፋ መሾሙን ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል

👉 “ውጤታማ የሆነው አሰልጣኝ ወደ ቡድናችን በመምጣቱ ደስ ብሎናል” አቶ ዓለማየሁ መንግሥቱ

👉 “ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ነበረበት ቦታ እና ዝናው ለመመለስ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ።” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

እንደቀደም ታሪካዊነቱ እና ዝናው ያለፉትን ዓመታት በመውጣት እና በመውረድ መካከል ውጣ ውረድ እያሳለፈ የሚገኘው አንጋፋው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ከፍተኛ ሊግ በወረደበት ዓመት ዳግም ለ2017 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደሚወዳደር እርግጥ ሆኗል።

ለከርሞ በአዲስ መልክ ቡድኑን አጠናክሮ ለመቅረብ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በዋና አሰልጣኝነት ከሳምንታት በፊት መሾሙ ሲገለፅ ሰንብቶ ዛሬ በራዲሰን ብሉ በተካሄደ የፊርማ ሥነ ሥርዓት እርግጥ ሆኗል። በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ዓለማየሁ መንግሥቱ ፣ የክለቡ የቦርድ አባላት፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ እና የደጋፊ ማኀበር አመራሮች በመርሐግብሩ ላይ ታድመዋል።

የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ዓለማየሁ መንግሥቱ የአሰልጣኙን ቅጥር አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “አሰልጣኝ ዘሪሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ በብዙ ስኬታማ ሥራዎቹ የምናውቀው አመለ ሸጋ በጣም ውጤታማ ከሚባሉት አሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው። ከእኛ ጋር ለመሥራት ፍቃደኛ በመሆኑ በጣም እናመሰግናለን። ደስም ብሎናል በማለት እንኳን ደኅና መጣ ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ትልቅ ታሪክ ያለው ቡድን ነው ፤ በዕድሜ ብንወስደው ከሀገሪቱ ክለቦች ሦስተኛ ነው። ብዙ ታሪክ ያለው ቡድን ነው። ይሄንን ቡድን ካለበት ከፍታ እና ዝቅታ ሁኔታዎች አሁን ወደ ከፍታው የተመለሰበት ጊዜ ነው። ይህን ከፍታ የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ በማለት ከገለጹ በኋላ የክለቡ ቦርዱ፣ ጽሕፈት ቤቱ አጠቃላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ቤተሰብ አንተ ውጤታማ እንድትሆን ሁሉም ከጎንህ ይሆናል በማለት በቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ መልካም ምኞታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በመቀጠል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በሰጠው አስተያየት “ወደዚህ ታሪካዊ ቡድን እንድመጣ ትልቁን ኃላፊነት አምናቹ ስለሰጣቹሁኝ ለክለቡ የቦርድ አባላት ክብር እና ምስጋና አቀርባለሁ ብሎ ከብዙ ውይይቶች በኋላ ወደዚህ ክለብ በመምጣቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ የሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳ፣ ከየትኛውም ክለቦች ያልተናነሰ ለብሔራዊ ቡድን ብዙ ተጫዋቾችን ሲያስመርጥ የነበረ ታሪካዊ ቡድን ነው ያለው አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር በሚኖረው የሁለት ዓመት ቆይታ ሊያሳካ ስለሚፈልገው ዕቅዱ ሲናገር

“ቡድኑን በሊጉ ለማቆየት እና በሂደት ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠራ አሁን ያለው የተጫዋቾች የዝውውር የፋይናንስ ስርዓት ካላገደን በቀር ጥሩ እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በማሰባሰብ ጥልቀት ያለው ቡድን በመሥራት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ነበረበት ቦታ እና ዝናው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ስኬታማ ቆይታ ካደረገበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር መለያየቱ ስለፈጠረበት ስሜት ሲናገር “ቅዱስ ጊዮርጊስ ከልጅነት እስከ እውቀት ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት ብዙ ድል ያጣጣምኩበት ቤቴ ነው። በዚህም ልክ ክብር እና ቦታ አለኝ አሁን ለሌላ ኃላፊነት ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጥቻለው። በቅዱስ ጊዮርጊስ ረጅም ዓመት ቆይታዬ የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረ መስቀል እኔን በማሳደግ ላደረጉልኝ ነገር በጣም አመሰግናለሁ። አጠቃላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ቤተሰቦች የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በሙሉ እጅግ አድርጌ ከልብ አመሰግናለሁ” በማለት ተናግሯል።

በማሳረጊያውም የፊርማ ሥነ ስርዓት እና የማሊያ ርክክብ ተካሂዶ ፕሮግራሙ ተገባዷል።