ምዓም አናብስት በሴራሊዮናዊ ግብ ጠባቂ ስብስቡን ማጠናከር ቀጥሏል።
ቀደም ብለው የነባሮቹን ውል በማራዘም ስምንት ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ሴራሊዮናዊውን ግብ ጠባቂ አልፋ ሴሳይ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በላይቤርያው ክለብ ሄቨን ኢለቨን ቆይታ የነበረው እና በውድድር ዓመቱ ‘የኢንተርቫርሲቲ’ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሽልማት ያሸነፈው ይህ ተጫዋች ከክለቡ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለመቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ከስምምነት ደርሷል።
የዌልሳዊው ክሬግ ቤላሚ ፋውንዴሽን ባቋቋመው ቶምቦ ሬንጀርስ የተባለ ክለብ የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው ግብ ጠባቂው ሬንጀርስ፣ ሪል ማክ እና በሴራሊዮን ዋናው ሊግ ተሳታፊ የሆነው ‘RSLAF’ (Republic of Sierra Leone Armed Forces FC) በተባሉ የሀገሩ ክለቦች ከተጫወተ በኋላ ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በላይቤሪያው ሄቨን ኢለቨን በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የወረቀት ሥራዎች በማገባደድ ላይ ይገኛል፤ በቀጣይ ቀናትም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ዝውውሩን ይቋጫል ተብሎ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ ሶፎንያስ ሰይፈ እና ሴራልዮናዊውን አልፋ ሴሳይ ለማስፈረም የተስማሙት መቐለዎች በቀጣይ አንድ ተጨማሪ ግብ ጠባቂ ወደ ስብስባቸው ይቀላቅላሉ ተብሎም ይጠበቃል።