ዐፄዎቹ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጀምረዋል

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 44 ነጥቦችን በመሰብሰብ 6ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ፋሲል ከነማዎች በተጠናቀቀው ዓመት በቡድኑ የነበሩ እና አዲስ የተቀላቀሉ ተጫዋቾችን በመያዝ ለ2017 ውድድራቸው ዝግጅታቸውን ለማድረግ ወደ አዳማ ከተማ አምርተው መቀመጫቸውን ሄልዝ ሆቴል ካደረጉ በኋላ ዛሬ ማለዳ አዳዲስ ፈራሚዎች የሜዲካል ቴስት ስለነበራቸው ባልተሳተፉበት ልምምድ በነባር ተጫዋቾች ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

ዛሬ ሐምሌ 29/2016 የቅድመ ውድድራቸውን በይፋ የጀመሩት ዐፄዎቹ ስብስባቸውን ለማጠናከር ናይጄሪያዊውን ግብ ጠባቂ ኦማስ ኦባሶጊ ፤ በረከት ግዛው እና አሚር ሙደሲርን ከፕሪምየር ሊግ ፣ ኃይሌ ዘመድኩን እና ቢኒያም ላንቃሞን ደግሞ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉ ሲሆን የአማካያቸውን አቤል እያዩን ውል ደግሞ ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል።