በተከታታይ ሦስት ዓመታት ሁለት ቡድኖችን ወደ ሊጉ ያሳደገው አጥቂ ውሉን ማራዘሙ ታውቋል።
ዳግም ወደ ሊጉ መመለሳቸውን ያረጋገጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተለያዩ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን ለማጠናከር እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል። ቡድኑ በከፍተኛ ሊግ በነበረው ቆይታ ጥሩ አገልግሎት የሰጠውን አጥቂ አቤል ሀብታሙ ውል አራዝሟል።
አቤል ሀብታሙ በጅማ አባጅፋር ከተጫወተ በኋላ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ዘመን ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲያድግ ቁልፍ ሚና የተወጣ ሲሆን ከቡድኑ ጋር በፕሪሚየር ሊጉ የስድስት ወር ቆይታ ካደረገ በኋላ በአጋማሹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመቀላቀል ንግድ ባንክ ወደ ሊጉ ሲያድግ ትልቅ አበርክቶ ነበረው። ዘንድሮ ዳግም ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተመለሰው አጥቂው ዳግመኛ ቡድኑን ማሳደግ ችሏል። በአስራ አንድ ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን መሸለም የቻለው አቤል ለሁለት ዓመት ከቡድኑ ጋር የሚያቆየውን ውል ማራዘሙ ታውቋል።