ብሩክ በየነ ነብሮቹን ለመቀላቀል ተስማማ

ሀድያ ሆሳዕና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹን በሁለት ዓመት ውል የቡድናቸው አካል ለማድረግ ተስማምተዋል።

የፕሪምየር ሊጉ ተካፋይ የሆነው ሀድያ ሆሳዕና ከአሰልጣኝ ግርማ ታደሠ ውል ማራዘም በኋላ የቃለአብ ውብሸት ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ መለሠ ሚሻሞ እና ሳሙኤል ዮሐንሰን ውል በማራዘም እንዲሁም ደግሞ እዮብ አለማየሁ ፣ በረከት ወንድሙ እና ጫላ ተሺታን ወደ ስብሰባቸው የቀላቀሉ ሲሆን አጥቂው ብሩክ በየነ ደግሞ አራተኛው ፈራሚ ለመሆን ከክለቡ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

ብሩክ ሀዋሳ ቄራ ሜዳ ላይ በነበረ የክረምት ውድድር በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ዕይታ ውስጥ በመግባቱ የክለብ ህይወትን በወልቂጤ የጀመረ ሲሆን በመቀጠል በሀዋሳ ከተማ እና ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና አሳልፎ ከሰሞኑ ከበርካታ ክለቦች ጋር ስሙ ቢያያዝም በዛሬው ዕለት በጥቅማጥቅም በተስማማበት እና በነገው ዕለት የሜዲካል ምርመራን በማድረግ ሀድያ ሆሳዕና ማረፊያውን አድርጓል።