ስሑል ሽረዎች የአጥቂ አማካይ ለማስፈረም ተስማሙ

ስሑል ሽረ ሁለገቡን የአጥቂ አማካይ ለማስፈረም ከጫፍ ሲደርስ የሁለት ነባር ተጫዋች ውል ለማራዘምም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

አምስት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምተው ከቀናት በፊት አስራ አንድ ነባር ተጫዋቾች ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በክለቡ ለማቆየት ውል ያራዘሙት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ አንድ ተጫዋቾች ለማስፈረም ከስምምነት ሲደርሱ የሁለት ተጫዋቾች ውል አራዝመዋል።


ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የማጥቃት ባህሪ ባላቸው ቦታዎች የሚጫወተው ኤልያስ አሕመድ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ከብርቱካናማዎቹ ጋር በነበረው ቆይታ በሀያ አምስት ጨዋታዎች ተሰልፎ 1754′ ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው ኤልያስ አሕመድ ላለፉት ቀናት ከቡድኑ ጋር ያደረገው ድርድር በስምምነት መገባደዱን ተከትሎ በቀጣይ ቀናት በይፋ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል ። ከዚ ቀደም በልደታው ኒያላ፣ ሐረር ሲቲ፣ ሰበታ ከተማ፣ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ በፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ለሆኑት ባህርዳር ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር፣ አዳማ ከተማና ድሬዳዋ ከተማ መጫወት የቻለው ተጫዋቹ የቡድኑ ስድስተኛ ፈራሚ ለመሆን ተቃርቧል።

ከሁለተኛ ቡድን የተገኘው የመሀል ተከላካዩ ሰለሞን ገብረክርስቶስ እና ጎይትኦም ነጋ ደግሞ በቡድኑ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት የተስማሙት ተጫዋቾች ናቸው። ጎይትኦም ነጋ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ ቡድን የተገኘና ከዚህ ቀደም ለጥቂት ጊዜያት ለሱዳኑ ሹርጣ አል ገዳሪፍ፣ ለትግራይ ውሃ ስራዎች ድርጅት፣ ለሱዳኑ ሞረዳ አል ገዳሪፍ እንዲሁም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በስሑል ሽረ ቆይታ የነበረው ሲሆን አሁን ደግሞ ከክለቡ ጋር ለመቀጠል ከስምምነት ደርሷል።