ያለፉትን ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ዋና ዳኛ በመሆን ያገለገለው ባለሙያ የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ሆኖ በይፋ ተሹሟል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በተከታታይ ዓመታት ላለመውረድ ከሚታገሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወልቂጤ ከተማ በ23 ነጥቦች 14ኛ ደረጃን በመያዝ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መሪነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን ለቀጣዩ የ2017 የውድድር ዘመን ደግሞ ወደ ዝውውር ከመግባታቸው በፊት አዲስ አሰልጣኝ በዛሬው ዕለት መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ያለፉትን ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በዋና ዳኝነት ያገለገለው ሶሬሳ ካሚል የቀድሞው ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት ተረክቧል። ከዚህ ቀደም ፊንጫ ስኳርን በአምበል እና በተጫዋችነት በመቀጠል ደግሞ ለሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ የተጫወተው አሰልጣኝ ሶሬሳ ካሚል ከእግርኳስ ከተገለለ በኋላ ወልቂጤ ከተማን በረዳት እና በዋና አሰልጣኝነት ሚዛን አማንን በተመሳሳይ በአንደኛ ሊጉ በዋና አሰልጣኝነት መርቷል። ከአሰልጣኝነቱ በኋላ በአንደኛ ሊጉ ፣ በከፍተኛ ሊጉ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመሐል ዳኝነት እየመራ የሚገኘው ሶሬሳ ካሚል ከዓመታት በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ተመልሶ የቀደመ ክለቡን ተረክቧል።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በሊጉ ስድስት ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት ሲመራ የተመለከትነው ሶሬሳ ካሚል ዳኝነትን በይፋ የሚያቆም መሆኑን እና ሙሉ ትኩረቱ ስልጠናው ላይ ብቻ እንደሚያደርግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።