የኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ውጪ ጨዋታን የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጪ ኬኒያ ፖሊስን ሲገጥም ጨዋታውን የሚመሩ አልቢትሮች ተለይተዋል።

አህጉራዊ የክለቦች ውድድር ከመጀመሩ በፊት የቅድመ ማጣሪያ ፍልሚያዎች ከቀናት በኋላ የሚጀምሩ ሲሆን በአዲስ መልክ ዘንድሮ የተከናወነው የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር አሸናፊው ኢትዮጵያ ቡናም በዚሁ የውድድር መድረክ ከኬኒያ ፖሊስ ጋር ጨዋታውን ለመከወን ቅድመ ዝግጅት ላይ ይገኛል።

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ ከአስር ቀናት በኋላ እሁድ ነሐሴ 12 በናይሮቢ ኒያዮ ብሔራዊ ስታዲየም (የተፈጥሮ ሳር ሜዳ) ሲደረግ ፍልሚያውንም የሚመሩ አልቢትሮችም ተለይተዋል። በዚህም የዲ አር ኮንጎ ዜግነት ያላቸው አራት ዳኞች ጨዋታውን እንዲመሩ ተመድበዋል።

ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ማሳንጉዌኒ ሉዊስ ሙዋምባ ሲመሩት ሙዋንያ ግራድል ቢሊዚ እና ኮላ አርቼንጅ ማታላታላ በረዳትነት እንዲሁም ይን ያኩዊስ ንጋምቦ ንዳላ በአራተኛ ዳኝነት ግልጋሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።