ያለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ከሰራተኞቹ ጋር ቆይታ የነበረው አማካይ ወደ ስሑል ሽረ ለማምራት ከስምምነት ደርሷል።
አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ቀጥረው ጋናዊው ተከላካይ ሱሌይማን መሐመድ፣ ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታ፣ ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ፋሲል አስማማው፣ ብርሀኑ አዳሙ፣ ኤልያስ አሕመድ እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ለማስፈረም ተስማምተው የአስራ ሦስት ነባር ተጫዋቾች ውል ያራዘሙት ስሑል ሽረዎች አሁን ደሞ ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በወልቁጤ ከተማ ቆይታ የነበረው የተከላካይ አማካዩ ሙሉዓለም መስፍን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
ወደ ክለቡ ለማምራት ተስማምቶ የህክምና ምርመራውን በማከናወን ክለቡን ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሰው ይህ ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዓመት ከሰራተኞቹ ጋር በነበረው ቆይታ በሀያ ስድስት ጨዋታዎች ተሳትፎ 1849′ ደቂቃዎች ቡድኑን አገልግሏል።
በአርባምንጭ ከተማ ከጀመረው የእግር ዖኳስ ህይወቱ በኋላ በሲዳማ ቡና ሁለት የውድድር ዓመታት ከዛ በመቀጠል በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቶ የፈረሰኞቹ የአራት ዓመት ቆይታው ካገባደደ በኋላም ወደ ቀድሞ ክለቡ ሲዳማ ቡና እንዲሁም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያሳለፈው አማካዩ የስሑል ሽረ የክረምቱ ስምንተኛ ፈራሚ ለመሆን ከጫፍ ደርሷል።