በአሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚመሩት አርባምንጭ ከተማዎች በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ያከናውናሉ።
ከፕሪምየር ሊጉ ለሁለት ጊዜያት ያህል ለመውረድ ከተገደዱ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው አርባምንጭ ከተማ በ2014 ከተሳተፈበት የሀገሪቷ ትልቁ የሊግ ዕርከን ከወረደ በኋላ በድጋሚ በዓመቱ በአሰልጣኝ በረከት ደሙ መሪነት ወደ ሊጉ ተመልሷል። ክለቡ በቀጣዩ ዓመት ተሳታፊ በሚሆንበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ አንድ ዓመት ውል ለነበረው ወጣቱ አሰልጣኝ ተጨማሪ አንድ ዓመትን ካከለ በኋላ ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት በማራዘም እንዲሁም ደግሞ ይሁን እንዳሻው ፣ ሙሉጌታ ካሳሁን ፣ ካሌብ በየነን እና ፋሪስ ዕላዊን ያስፈረሙ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ከሀገር ውስጥ ከውጪ ሀገር ከሚያስፈርሟቸው ተጫዋቾች በፊት ቡድኑ ዝግጅት ለመጀመር ማቀዱን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።
እንደ ክለቡ ገለፃ ከሆነ የተጫዋቾች ማረፊያ (ካምፕ) ዕድሳቱ በመጠናቀቁ የቡድኑ አጠቃላይ አባላት የፊታችን ዕሁድ ከተሰባሰቡ በኋላ በማግስቱ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 በይፋ በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።