ጎፈሬ ከዩጋንዳው ኤክስፕረስ ክለብ ጋር ስምምነት ፈፀመ

ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከአንጋፋው የዩጋንዳ ክለብ ኤክስፕረስ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፀመ።

ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከሀገር ውስጥ ደንበኞቹ አልፎ ምህዳሩን በምስራቅ አፍሪካ እያሰፋ የሚገኝ ሲሆን በተለይ በዩጋንዳ ያለውን ተደራሽነት አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ስምምነት በዛሬው ዕለት ፈፅሟል። በዚህም ከዩጋንዳው አንጋፋ ክለብ ኤክስፕረስ እግርኳስ ክለብ ጋር ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሟል።

ቀትር ላይ በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ስርዓት የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም የኤክስፕረስ እግርኳስ ክለብ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ ሚስተር አሽራፍ ሚይሮ የተገኙ ሲሆን ስምምነታቸውን በፊርማቸው ከማረጋገጣቸው ጎን ለጎን ስለውሉ ዝርዝር ጉዳዮችን በስፍራው ለተገኙ የተለያዩ አካላት አብራርተዋል።

በቅድሚያ መድረኩን በንግግራቸው የጀመሩት አቶ ሳሙኤል ድርጅታቸው እየተከተለ ባለው አዲስ ስትራቴጂ መሠረት ክለቦች ከጎፈሬ ጋር በአሰራር እና በአስተሳሰብ አብረው የሚሄዱ ሆነው ሲገኙ ስምምነቶችን እንደሚፈፅሙ አውስተው ከውጤታማው የዩጋንዳ ክለብ ጋር ለመስራት በመቻላቸው ደስተኛ እንደሆኑ አመላክተዋል። አቶ ሳሙኤል ጨምረውም ይህ ስምምነት ጎፈሬ በዩጋንዳ ባለው መጠነ ሰፊ ስራ መነሻነት ክለቡ ራሱ ጎፈሬን መርጦ እንደመጣ ጠቁመዋል።

የቀድሞ አልቢትር እና የአሁኑ የኤክስፕረስ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ ሚስተር አሽራፍ ሚይሮ በበኩላቸው በጎፈሬ አማካኝነት ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው የስፖርት ብራንዱ በዩጋንዳ እጅግ እየታወቀ በመምጣቱ አብረው ለመስራት እንደወሰኑና በሁለት ቀናት ናሙናዎችን አይተው በጥራትም በምርት አቅርቦትም ደስተኛ በመሆናቸው የሦስት ዓመት ውል ለማሰር መወሰናቸውን ገልፀዋል።

ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ በተገለፀው የ36 ወራት የጊዜ እርዝማኔ ለወንዶች፣ ለሴቶች እና ለታዳጊዎች ቡድኖች ሙሉ ትጥቆችን በስፖንሰርሺፕ እና ቅናሽ እንዲሁም በአጠቃላይ ከ30 ሺ በላይ የደጋፊዎች ማሊያ እንደሚያቀርብ ተነግሯል።

የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ እና የፎቶ ፕሮግራም ከተከናወነ በኋላ አቶ ሳሙኤል በቀጣይ ቀናት ሌሎች በርካታ ታላላቅ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ስምምነቶችም እንደሚያበስሩ ጠቁመዋል።