የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በሶዶ ከተማ የጀመሩት የጦና ንቦቹ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ለመፈፀም ተስማምተዋል።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በሶዶ ከተማ ከነሐሴ 2 ጀምሮ መከወን የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ለቀጣዩ የውድድር ዘመን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሙሉቀን አዲሱ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሠ ፣ ውብሸት ክፍሌ ፣ መሳይ ሠለሞን ፣ ምንተስኖት ተስፋዬ እና ያሬድ ዳርዛን የስብሰባቸው አካል ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን የስብሰባቸው አካል በማድረግ የአዳዲስ ፈራሚ ቁጥራቸውን ስምንት አድርሰዋል።
ተስፋዬ መላኩ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል። በወላይታ ድቻ የዛሬ ስምንት ዓመት ተጫውቶ የነበረው እና በአማካይ እንዲሁም በተከላካይ ቦታ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ በመቀጠል በኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ጅማ አባቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ በወልቂጤ ከተማ አሳልፎ ወደ ቀድሞው ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር አገባዷል።
ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እየቀረው በስምምነት የተለያየው ካርሎስ ዳምጠውም ሶዶ ደርሷል። ከነገሌ አርሲ የእግር ኳስ ህይወቱን በመጀመር ለመቻል ፣ አውስኮድ ፣ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ወልዋሎ ፣ ጅማ አባቡና እና ለገጣፎ ለገዳዲ በተከላካይ በአማካይ እና በአጥቂነት የተጫወተው ግዙፉ ተጫዋች በድሬዳዋ ከተማ የአንድ ዓመት ቆይታን አድርጎ ወደ ወላይታ ድቻ አምርቷል።