አሰልጣኝ ገብረክርሰረቶስ ቢራራ ምክትላቸውን አሳውቀዋል

ቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አብረዋቸው የሚሰሩትን ምክትል አሰልጣኝ አሳውቀዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ጊዜ መቻልን ከባለፉት ዓመታት በተሻለ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ አቆይተው በሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲጠናቀቅ ያስቻሉት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ከቡድኑ ጋር የሚቆዩበትን ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።

ያለፈውን አንድ ዓመት በረዳት አሰልጣኝነት አብረዋቸው የሰሩት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ ወደ መቐሌ ማምራታቸውን ተከትሎ የምክትል አሰልጣኝ ቦታቸው ክፍት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ መነሻነት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ለክለቡ ቦርድ በቀጣይ ጊዜያት በረዳትነት አብረዋቸው እንዲሰሩ አሰልጣኝ ደምስ ፈቃዱን ያሳወቁ ሲሆን ክለቡም የአሰልጣኙን ጥያቄ ተቀብሏል።


አሰልጣኝ ደምስ ፈቃዱ በስልጠናው ዓለም ረዘም ላሉ ዓመታት የቆዮ ሲሆን በተለይ በተስፋ ቡድኖች ላይ የሰሩ ሲሆን በማስከተል በአዲስ አበባ ከተማ ረዳትና ዋና አሰልጣኝ ሆነው መስራታቸው ሲታወቅ በከፍተኛ ሊግ ንብን በመያዝ ማሰልጠን ችለዋል።