ኃይቆቹ ዝግጅት ማድረግ ሊጀምሩ ነው

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሊከውኑ ነው።

የ2016 የውድድር ዘመናቸውን በ41 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ የፈፀሙት ሀዋሳ ከተማዎች በቀጣዩ የውድድር ዘመን የተሻለ ተሳትፎ ለማድረግ በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስከ አሁን ቢኒያም በላይ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ እና ሰይድ ሀብታሙን የግላቸው አድርገው የእስራኤል እሸቱ እና ምንተስኖት ጊምቦን ውል ደግሞ ለተጨማሪ ዓመት ማደሳቸው የሚታወስ ሲሆን ቡድኑ በቀጣዮቹ ቀናት ከሚያስፈርማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ማድረግ እንደሚጀምሩ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ ተመላክቷል።


የቡድኑ አባላት በዛሬው ዕለት የተሰባሰቡ ሲሆን ማረፊያቸውን ሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል አድርገው ከነገ ዕሮብ ነሐሴ 8/2016 ጀምሮ በሀዋሳ እና በወንዶ ገነት እያፈራረቁ ዝግጅታቸውን ማከናወን ይጀምራሉ።