አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ረዳታቸውን አሳውቀዋል።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ መሪነት የ2017 የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በትላንትናው ዕለት መቀመጫቸውን በአዳማ ከተማ በማድረግ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረሟቸውን ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾች ጨምሮ ነባሮቹንም በማቀፍ የሁለተኛ ቀን ልምምዳቸውን በዛሬው ዕለትም አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን አዲሱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለም በአዳማ ከተማ አብሮት የሰራውን አሰሎጣኝ ተረፋ ሂርጳሳን የቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ በማድረግ እንዲያገለግል መርጠውታል።
የክለቡ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የተሾመው ተረፋ ሂርጳሳ በኦሮምያ ፓሊስ ውስጥ የተጫዋችነት ዘመንን ያሳለፈ ሲሆን በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ገላን ከተማ ለአምስት ዓመታት ረዳት አሰልጣኝ እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በአዳማ ከተማ የይታገሱ እንዳለ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ሲያገለግል ቆይቶ በተመሳሳይ በድሬዳዋም ከአሰልጣኙ ጋር በጋራ ለመስራት ወደ ድሬዳዋ አምርቷል።
ከአዲሱ ረዳት አሰልጣኝ ተረፈ ሂርጳሳ በተጨማሪ አለምሰገድ ወልደማርያም እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ መሐመድ ጀማል እንዲሁም የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ዚያድ ሁሴን በክለቡ እንዳሉ ሆነው እንደሚቀጥሉ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።