በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክለው ንግድ ባንክ ከሜዳ ውጭ ለሚያደርገው ጨዋታ ነገ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ታውቋል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከረጅም ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን በመወከል በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ቻምፕዮንስ ሊጉ የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከዩጋንዳው ዩ ኤስ ቪታ ጋር መደልደሉ ይታወቃል።
ለዚህም ይረዳው ዘንድ ከሐምሌ የ25 ቀን ጀምሮ በአዳማ ከተማ መቀመጫውን በማድረግ ዝግጅቱን እያደረገም ቆይቷል። የሀገር ቤት ልምምዱን ነገ ማለዳ በዛው በአዳማ ሰርቶ ካገባደደ በኋላ የአሰልጣኝ አባላቱን ጨምሮ 25 ተጫዋቾቹን በጠቅላላ በመያዝ ከሰዓት ወደ ዩጋንዳ የሚጓዝ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣይ ቅዳሜ ከዩጋንዳው ዩ ኤስ ቪታ ጋር አመሻሽ ላይ የሚጫወት ሲሆን ጨዋታውም በካምፓላ በሚገኘው ናምቡሌ ስቴድየም አድርጎ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ በሳምንቱ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል።