ፈረሰኞቹ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሊጀምሩ ነው

የቀድሞው አሰልጣኛቸውን ዳግም ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በቢሾፍቱ ከተማ ማከናወን ይጀምራሉ።

ያለፈውን የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ዓመቱን አገባደው በመጨረሻም በጊዜያዊ አሰልጣኙ ደረጀ ተስፋዬ ማጠናቀቅ የቻሉት እና በደረጃ ሰንጠረዡ በ48 ነጥቦች አምስተኛ ላይ ተቀምጠው መቋጨት የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለ2017 የውድድር ዘመን የቀድሞው ተጫዋቻቸውን እና አሰልጣኝ በመሆንም ጭምር ያገለገለውን ፋሲል ተካልኝ በሀላፊነት መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን በዝውውሩ ላይ በመሳተፍ ባደረጉት ጥቂት ተሳትፎ እንደ ፍፁም ጥላሁንን ከፕሪምየር ሊጉ ፣ ፓውሎስ ከንባታ እና ፀጋ ከድርን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ስብሰባቸው የቀላቀሉ ሲሆን በቀጣይ ከሚያደርጉት የተጨማሪ ተጫዋቾች ፊርማ በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ማከናወን እንደማጀምሩ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ መረጃ ደርሷታል።

የቡድኑ አባላት በዛሬው ዕለት ቢሾፍቱ በሚገኘው የክብር ይድነቃቸው ተሠማ አካዳሚ ከተሰባሰቡ በኋላ ከነገ ዕርብ ነሐሴ 10/2016 ጀምሮ በይፋ ዝግጅታቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።