አማካዩ ወደ እናት ክለቡ ለመመለስ ተስማማ

ቀደም ብለው በርከት ያሉ ዝውውሮችን ያገባደዱት ስሑል ሽረዎች ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለውበታል።


በዝውውሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ቡድናቸውን  በማጠናከር ላይ ያሉት እና ከቀናት በፊት በደሴ ከተማ ቆይታ የነበረው አዲስ ግርማን በአንድ ዓመት ውል ወደ ቡድናቸው የቀላቀሉት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ የቀድሞ ተጫዋቻቸውን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።


ያለፈውን አንድ ዓመት ከስድስት ወር በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይታ የነበረው እና ቡድኑ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ትልቅ ድርሻ ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ነጻነት ገብረመድኅን ወደ አሳዳጊ ክለቡ ስሑል ሽረ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል። በ2013 መጀመሪያ ላይ ለዓመታት የተጫወተበትን አሳዳጊ ቡድኑ ስሑል ሽረን ለቅቆ መቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ተስማምቶ የነበረው ተጫዋቹ ክለቡ በአስከፊው ጦርነት ምክንያት ከውድድር መራቁን ተከትሎ በመቐለ መለያ ጨዋታ ሳያከናውን መለያየቱ ሲታወስ በሁለት የተለያዩ መንፈቆች ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን በፕሪምየር ሊጉ መወከሉ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ከውጤታማ የአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊጉ ቆይታ በኋላ ዳግም በፕሪምየር ሊጉ ለመጫወት ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ስሑል ሽረ ተመልሶ ለመጫወት ከጫፍ ደርሷል። በአማካይነት እና በመሃል ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ሁለገቡ ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዓመት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተከትሎ በከፍተኛ ሊጉ ምርጥ ቡድን መካተቱ ይታወሳል።