ኢትዮጵዊያን ዳኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርተዋል

አራት ኢትዮጵያዊያን ዓለም አቀፍ ዳኞች ፕሪቶሪያ ላይ የሚደረገውን የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ

የ2024/25 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ የአህጉሩ ሀገራት መደረግ ይጀምራሉ። አርባ ስምንት ክለቦች ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ ተሳታፊ በሚሆኑበት መድረክ ሀገራችን ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምትወከል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አራት ኢትዮጵያን ዳኞች ደቡብ አፍሪካ ላይ የሚደረግ የማጣሪያ ጨዋታን እንዲመሩ በካፍ መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

የኢሲዋቲኒው ክለብ የሆነው ማባባኔ ሱዋሎስ ሀገሪቱ የፊፋ እና የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ሜዳ የሌላት በመሆኑ በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ በሚገኘው ሉካስ ሞሪፒ ስታዲየም ላይ የሞዛምቢኩን ክለብ ፌሮፊያሪዮ ዳ ቤሪራን የፊታችን ዓርብ ነሐሴ 10 ምሽት 2 ሰዓት ላይ የሚያስተናግድ ሲሆን በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመድረኩ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞቹ ትግል ግዛው እና ፋሲካ የኋላሸት ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለማገልገል ወደ ስፍራው አምርተዋል።