አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ምክትሎቻቸውን አሳውቀዋል

በመቀመጫ ከተማቸው ዝግጅታቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ አብረዋቸው የሚሠሩትን ምክትሎቻቸውን አሳውቀዋል።

ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ለቀጣዮቹ ዓመታት አብሮ ለመሥራት ፊርማቸውን ያኖሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ አብረዋቸው የሚሠሩ ረዳቶቻቸውን በአዲስ መልክ አዋቅረዋል። በረዳት አሰልጣኝነት ካሊድ መሐመድ እና መስፍን አህመድን እንዲሁም የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እንዲሆኑ ኢያሱ ደስታን መምረጣቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አሰልጣኝ ካሊድ መሐመድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ሲሆን ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት በኢትዮጵያ ቡና በምክትል እና በዋና እንዲሁም በዳሽን በማስከተል ወደ ከፍተኛ ሊግ በማምራት ያለፉትን አምስት ዓመታት ቡታጅራ ከተማ፣ ሀላባ ከተማ እና ወልዲያ ከተማ መሥራታቸው ይታወቃል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና በኋላም ወደ አሰልጣኝነት ህይወት የገባው መስፍን አህመድ አብዛኛውን የስልጠና ህይወቱን በኢትዮጵያ መድን ከ17-20 ዓመት በታች ቡድኖች በዋና አሰልጣኝነት የሠራ ሲሆን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን የመጀመርያ ሥራውን የሚጀምር ይሆናል።

የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ኢያሱ ደስታ በአየር ኃይል፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኒያላ ፣ ሻሸመኔ ከተማ በግብ ጠባቂነት ያሳለፈ ሲሆን ወደ ስልጠናው በመግባት በወላይታ ድቻ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና በሰበታ ከተማ የሠራ ሲሆን አሁን ደግሞ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ መመለሱ ታውቋል።

አዲስ የተሾሙት አሰልጣኞች ከቡድኑ ጋር ቅድመ ውድድር ዝግጅት አብረው መሥራት መጀመራቸውንም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።