በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ ተገልፆ የነበረው የሴካፋ ውድድር የመክፈቻው ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም መዞሩ ታውቋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር በነገው ዕለት ይጀመራል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ የሌሎች ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ክለቦች ለውድድሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸውን አዲስ አበባ በመግባት እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ግን የዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ ነገ የመክፈቻ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት እስካሁን አዲስ አበባ አልገባም።
በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውድድሩ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ ቢገልፅም አሁን በተገኘ መረጃ ነገ 7 እና 10 ሰዓት የሚደረጉት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከወናሉ።