“ሁሉም ደጋፊዎች ነገ ንግድ ባንክን እንዲደግፉ ጥሪ አቀርባለሁ” አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው

👉 “ከባለፉት ውድድሮች ተምረን ውጤታማ ለመሆን እንጥራለን።”

👉 “የእኛ ተጫዋቾች መውጣት ቢፈልጉ እና ነገሮች ቢመቻቹ ‘ፕሮፌሽናል’ መሆን ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው።”

👉 “ውድድሩ ወደ ሀገር መምጣቱ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው።”

የሴካፋ ዞን የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ከነገ ነሐሴ 11 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 26 በመዲናችን አዲስ አበባ በስምንት ቡድኖች መካከል የሚደረግ ሲሆን ሀገራችንን የሚወክለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በምድብ አንድ ተደልድሎ ነገ 10 ሰዓት ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከራየን ስፖርት ጋር የሚያደርግ ይሆናል። የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ዝግጅት እንዴት ነው?

ዝግጅት በጣም ቆንጆ ነው፤ አዳማ ሁለት ሳምንት ተዘጋጅተናል። አዲስ አበባ ከመጣን ሦስት ቀን ሆኖኗል። ውድድራችን ደግሞ አዳማ እና ሀዋሳ ነበር። አዲስ አባበ በምንመጣበት ጊዜ የአየር ለውጥ ይኖራል ብዬ አስባለው።

በሀገራችን ለሚደረገው ውድድር ምን የተለየ ዝግጅት አደረጋችሁ?

ውድድሩ በሀገራችን መካሄዱ በጣም ጥሩ ነው። ይሄ ለወጣቶች ይበልጥ መነቃቃት ይፈጥራል። በደጋፊያችን ፊትም ስለምንጫወት በዝግጅቱም የተወሰነ ነገር ለመስራት ወስነናል።

በዝውውር መስኮቱ ቡድኑ ራሱን አጠናክሯል። ቡድኑ በምትፈልገው መንገድ ሙሉ ነው?

በዝውውር በኩል በደንብ ነው የተሳተፍነው፤ በርግጥ ከዚህ በፊት ያጣናቸው ተጫዋቾች አሉ። ወደ ያንግ አፍሪካ የፈረመችው አርያት ኦዶንግ፣ ሎዛ አበራ እንዲሁም መዲና ዐወል እና ኚቦኝ በጉዳት ላይ ነው የሚገኙት፤ በእነሱ ምትክ ደግሞ ወጣት እና ታዳጊዎች ወደ ክለቡ ቀላቅለናል። ክፍተቱን ይሞላሉ ብለን እናስባለን። እነዚ ታዳጊዎች ነገም ለሀገር የተሻለ ስራ መስራት የሚችሉ ናቸው።

ባለፉት ሶስት ተከታታይ ውድድሮች ቡድኑ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። ዘንድሮስ ምን እንጠብቅ?

ላለፉት ሦስት ዓመታት አመርቂ ውጤት አስመዝግበናል፤ በተለይም በመጀመርያው የኬንያ እስከ ጫፍ ድረስ ሄደን በመጨረሻው ዘጠና አራተኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብን ነበር። የዛን ጊዜ ያነበሩብን ችግሮች ከጨዋታ ጨዋታ የመዳክም ችግሮች ነበሩብን። ከተቀሩት የምስራቅ አፍሪካ ቡድኖች የኳስ ቅብብሎችን እጅግ የሚደነቅ ነው። ታንዛንያ በነበረውም ሦስተኛ ደረጃ ይዘን ነው የመጣነው፤ በርግጥ በውጤት ቀንሰናል በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን የተሻሉ ነገሮች አሳይተናል። በመጨረሻው የዩጋንዳ ውድድርም በመለያ ምት ነው የወደቅነው፤ በዘንድሮው ከሦስቱም ውድድሮች ተምረን ውጤታማ ለመሆን የበለጠ እንጥራለን። ከዚህ በፊት ደረጃ ውስጥ ገብተን ነበር፤ መታወቅ ያለበት ነገር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዋርየር የሚባለው የዛንዚባር ቡድን እና የጅቡቲው ክለብ እስካሁን ባለኝ መረጃ ከዘጠኙ ሀገር በቀል ተጫዋቾች የያዙ ክለቦች ናቸው፤ ይሄ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው። የእኛ ተጫዋቾች መውጣት ቢፈልጉ እና ነገሮች ቢመቻቹ ‘ፕሮፌሽናል’ መሆን ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው። ከባለፉት ውድድሮች ተምረን ውጤታማ ለመሆን እንጥራለን።

በሀገር ሜዳ በደጋፊ ፊት መጫዎት ያለውን ጥቅም በምን ያህል ደረጃ ለመጠቀም አስባችኋል?

በቅርብ ጊዜ በሀገራችን በደጋፊ ፊት የመጫወት ዕድል አልነበረም፤ አሁን መምጣቱ እጅግ ነው የሚያስደስተው፣ የሚያኮራውም። በእኔ በኩል በጣም ተደስቻለሁ፤ ውድድሩ በሀገራች እንዲዘጋጅ ያደረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽንም እናመሰግናቸዋለን። አሁን ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ከመጣን በኋላ ሁሉም አመራሮች በተገቢው ሁኔታ እያገዙን ነው። ወደዚ መምጣቱ በአየር ሁኔታውና ክረምት በመሆኑ ልንቸገር እንችላለን እንጂ በአጠቃላይ ውድድሩ ወደ ሀገር መምጣቱ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው።

ለደጋፊዎች የምታስተላልፉት መልዕክት ካለ?

ቡድናችን አሁን ያለበት ሁኔታ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ወጣት እና ታዳጊዎች እንዲሁም ከሌሎች ክለቦች የመጡትን እያቀናጀን እንገኛለን። ደጋፊ በተመለከተ ማንሳት የምፈልገው ሀዋሳ እና አዳማ ብዙ ደጋፊ አልነበረንም ግን በመጨረሻ የነበረን ደጋፊ ሳስበው ስመኘው የነበረ ነው። በጣም ከመጠን በላይ ደጋፊ እያዜመልን ነበር፤ የቡና ወይ የጊዮርጊስ ነው ተሳስቼ ነው እንዴ ብዬ ዞር ብሎ እስከማየት ደርሻለሁ። ቡድናች በወንዶችም የሴቶቹም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በዛ ደረጃ ሲደገፍ ማየት እጅግ ደስ ይላል። ሞራላቸው ከሚገባው በላይ ነበር፤ ይሄ ደግሞ የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ ውድድርም ስለሆነ የዛን ጊዜ የደገፈን ደጋፊ እንዲመጣ ደጋፊ እንደ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ስለሆነም ለክለባችን የበለጠ ጥንካሬ ይሰጣል እና ሁሉም ደጋፊዎች ነገ ንግድ ባንክን እንዲደግፉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።