በነገው ዕለት በካፍ ኮፌዴሬሽን የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ኬኒያ ያቀኑት ቡናማዎቹ የግብ ጠባቂያቸውን ግልጋሎት እንደማያገኙ ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ቡናማዎቹ ከኬኒያው ኬኒያ ፖሊስ ጋር የመጀመሪያ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ናይሮቢ ላይ ለማከናወን ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች አስራ ስምንት ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ካይሮ ቢያቀኑም አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ግብ ጠባቂው ኢብራሂም ዳንላድ ከጨዋታው ውጭ መሆኑን ሰምተናል።
ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቹን ለማስፈረም አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቲኤም ኤስ ማኔጀር ጋር በመሆን ግብ ጠባቂው የሚመዘገብበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻልም የጋና እግርኳስ ፌዴሬሽን ተጫዋቹን ለማስመዝገብ በሚደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው የካፍ ስም ዝርዝር የሚላክበት ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ ትናንት ማምሻውን አስፈላጊዎቹን ቅድመ ሁኔታዎችን ቢፈፅሙም ግብ ጠባቂው ስሙ በካፍ ዝርዝር ውስጥ አለመካተቱን ተከትሎ ከቡድኑ ጋር አብሮ ወደ ኬኒያ ቢጓዝም ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ እርግጥ ሆኗል። ምን አልባት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከካፍ ጋር በኢሜል ንግግሮችን እያደረገ መሆኑን ተከትሎ የሚሳካ ከሆነ የመጫወት እድል ሊኖረው እንደሚችል ሰምተናል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል በጉዳዩ ዙሪያ ለቲ ኤም ኤስ ማኔጀር እና ለክለቡ ህዝብ ግንኙነት አቶ ዮሐንስ መረጃ ለማግኘት ደውለን እንደነገሩን ከሆነ “በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ካፍን ጨምሮ ንግግር እያደረግን ስለሆነ አሁን ላይ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንቸገራለን” ሲሉ ገልፀውልናል።
ግብ ጠባቂው ኢብራሂም ዳንላድ የሚደረገው ጥረት የማይሳካ ከሆነ በመልሱ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያውን ዙር በደርሶ መልስ የሚያልፍ ከሆነ በሁለተኛው ዙር ከዛማሊክ ጋር ለሚኖረው ጨዋታ የሚደርስ እንደሆነ አውቀናል።