የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ራዮን ስፖርትን 3ለ2 በመርታት ውድድሩን በድል ጀምሯል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ጅምሩን ያደረገው የሴካፋ ዞን የካፍ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያን የወከለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርት ያገናኘ መርሐግብር ነበር። 9 ሰዓት ሲል ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ ጅምሩን አድርጎ 27ኛው ሰከንድ ላይ እንደደረሰ ሰናይት ቦጋለ ከመሐል ክፍሉ ወደ ግራ በአግባቡ ያቀበለቻትን ኳስ ንግሥት በቀለ በጥሩ ዕይታ የሰጠቻትን ሴናፍ ዋቁማ ከመረብ አሳርፋ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች።
ጨዋታውን በመቆጣጠር በኮሪደሮች በኩል በይበልጥ የፈጣን አጥቂዎቻቸውን ግልጋሎት በተደጋጋሚ ያገኙ የነበሩት የአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተጫዋቾች በንግሥት ፣ ሴናፍ እና አረጋሽ ጥምረቶች በድግግሞሽ የራዮን የሜዳ ክፍልን ሲረብሹ ተስተውሏል። በተጋጣሚያቸው በብዙ መልኩ የተበለጡት በአሰልጣኝ ራዋካ ክላውዲ የሚመሩት ራዮን ስፖርቶች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ወደ አቻነት ለመምጣት ጥረት ሲያደርጉ መመልከት ቢቻልም ቡድኑ ከቀኝ በኩል ከተሻገረ ኳስ ሁዋሴ አንደርሰኔ በግንባር ገጭታ ዒላማዋን ሳትጠብቅ ከወጣችዋ ኳስ ውጪ በአብዛኛው በንግድ ባንክ ብልጫ ተወስዶባቸው ተመልክተናል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሲቃረብ በጨዋታው ደምቃ የታየችው አረጋሽ ካልሳ ከመሳይ ተመስገን የደረሳትን ኳስ ከግራ በኩል በግምት 25 ሜትር ርቀት ላይ የግብ ዘቧን ናዳኪማና አንጄሊኔ አቋቋም ተመልክታ እጅግ ግሩም ግብ አክላ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ0 መሪነት ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ አጋማሹ በጀመረ 47ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች በአንድ ሁለት ጥሩ ቅብብል ሰናይት እና አረጋሽ ካደረጉ በኋላ በመጨረሻም አረጋሽ ካልሳ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛውን ግብ ከመረብ አዋህዳለች። ሦስት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ በሽግግር የጨዋታ መንገድ ወደ ውስጥ በሚሻገሩ እና ከቆሙ ኳሶች ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ራዮን ስፖርቶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ግብ አግኝተዋል።
65ኛው ደቂቃ ላይ ሀሳቤ ሙሶ ሁሙሆዛ አንጄሊኪ ላይ የሠራችውን ጥፋት ተከትሎ በሳጥኑ ጠርዝ የተገኘን የቅጣት ምት ኡኩዌንኩንዳ ያኔቲ አክርራ በመምታት የግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ስህተት ታክሎበት ኳስን ከመረብ አገናኝታለች። ግብን ካገኙ በኋላ በተሻለ ተነሳሽነት መጫወታቸውን የቀጠሉት ራዮኖች ከ12 ደቂቃዎች በኋላም ሁለተኛ ጎል ሲያስቆጥሩ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ሁዋሴ አንደርሰኔ በግንባር ገጭታ የንግድ ባንክ ተከላካዮች ያገኙትን ኳስ ከራስ ሜዳ በአግባቡ አለማፅዳታቸውን ተከትሎ ጂያኔ ሙካንዳይሴኔ ጨዋታውን ወደ 3ለ2 ያደረገች ጎልን አስቆጥራለች።
ንግድ ባንኮች በፈጣን ሽግግር በርካታ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም አረጋሽ ፣ ሴናፍ እና ንግሥት ያለቀላቸውን ዕድሎችን መጠቀም ላይ ዐይናፋር ሆነው ታይተዋል ፣ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በቀሩት አምስት ያህል ደቂቃዎች ብልጫን የወሰዱት ራዮኖች ቢሆኑም እንዳገኙት ዕድሎች ተጨማሪ ግብን ማከል ሳይችሉ በ3ለ2 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተቋጭቷል።