የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-2 ራየን ስፖርትስ

👉 “ሦስት ጎል ቀድመን ስላገባን የተወሰነ መዘናጋት ነበር።” አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው

👉 “ቡድናችን ከተመሠረተ ሁለት ዓመቱ ስለሆነ ፤ በዚህ መድረክ መሳተፋችን በራሱ ትልቅ ስኬት ነው።” ርዋካ ክላውዲ

ዛሬ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተጀመረው የሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ራየን ስፖርትስን 3ለ2 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች ጋር ተከታዩን የጥያቄ እና መልስ ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው…

“አጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል። ከዕረፍት መልስ የተወሰነ መቀዛቀዝ ነበር ፤ የጌሙ ባሕሪ ነው ፣ ጨዋታው ሲያልቅ ነው ሁሉም የሚታወቀው። ሦስት ጎል ቀድመን ስላገባን የተወሰነ መዘናጋት ነበር እና መዘናጋት ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል። ሆኖም ግን እስከብዙ ችግሮች የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፍ ቲሙን ከፍ ያደርጋል።”

ይታዩ ስለነበሩ የጨዋታ መቆራረጦች…

“የጨዋታው ባሕሪ አሰቸጋሪ ነው። 15 ቀን ነው የተዘጋጀነው በዛም ምክንያት መቆራረጦች ነበሩ። አዳዲስ ተጫዋቾች አሉ እነሱን ደግሞ በወዳጅነት ጨዋታ አልገነባንም ፤ ወቅቱ ክረምት ስለሆነ በቂ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አላገኘንም ። 8 አዳዲስ ተጫዋቾትን አስገብተናል እና የተወሰኑ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይከሰታሉ። መቆራረጦች ይኖራሉ ፤ የተሟላን ነን ብዬም አላስብም። ጨዋታውን ለማስጠበቅ ሲባል እመቤት አዲሱ በተወሰነ መልኩ ወደ ተከላካዮች ጋር መሄድ ስለጀመረች በዛ ምክንያት ደግሞ መሃሉ ሳሳ ብሏል። እስከዚህ ችግር በማሸነፋችን ግን የተወሰኑ ችግሮችን እንቀርፋለን ብዬ አስባለሁ።”

በተደጋጋሚ ጊዜያት ከቆሙ ኳሶች የሚያስተናግዷቸው ግቦች ስላለመሻሻላቸው እና ስለሚባክኑ የግብ ዕድሎች…

“እነዚህ ነገሮች ላይ እንደ ሀገርም ችግሮች አሉብን። በወንዶችም በሴቶችም አጠቃላይ በቆሙ ኳሶች ችግሮች አሉብን እና ግን ከዚህ በኋላ እያስተካከልን መሄድ አለብን። ላለፉት አራት ዓመታት እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን አስተናግደናል ፣ ይህንንም በሂደት እናስተካክላለን ብዬ ነው የማስበው። በባከኑ የግብ ዕድሎች ስለተነሳው ጥያቄ መጓጓት ስላለ ዛሬ እግዚአብሔር ይመስገን ሦስት ጎል ቀድመን ባናስቆጥር ኖሮ ማሸነፋችን ጥርጣሬ ውስጥ ይገባ ነበር እና ንግሥትም አዲስ ነው የመጣችው እንደገና ደግሞ ሴናፍም ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበረች ፤ አረጋሽም በተወሰነ መልክ። የቲሙ ተብላልቶ መቀናጀት ጌሙ ራሱን በራሱ እያስተካከለ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ። ቀጣይ ግን እነዚህን ነገሮች እየቀረፍን እንሄዳለን።

ተመሳሳይ ባሕሪ ያላቸውን ተጫዋቾች አንድ ላይ ስለመጠቀማቸው (ለምሳሌ ተቀይረው የገቡት ሲሣይ እና ብርቱካን)…

“እግርኳሳዊ ነው በነገራችን ላይ በአሰልጣኝም በተጫዋችም በተወሰነ መልኩ ችግሮች ይኖራሉ። ለቀጣይ ስለሚጠቅመን በሚገባ እናርመዋለን ብዬ አስባለሁ። በተቃራኒው ግን አስቤው የነበረው ተቃራኒ ቡድን በተወሰነ መልክ መሃል ላይ ኳስ ስትይዝባቸው ቦታ የመሳሳት ነገር ይታይባቸው ነበር እና ተጫዋቾቻችን ደግሞ በተፈጥሯቸው ኳስን የሚይዙ ስለነበሩ ነው። እንደተባለው ግን አንድ ሰው መሃላቸው ቢገባ ነገሮችን መለወጥ ይችላል።”

ከጨዋታው በፊት ስለተጋጣሚያቸው ስለሰበሰቡት መረጃ እና በ20 ሴኮንዶች ውስጥ ጨዋታውን መምራት ስለመጀመራቸው…

“በተወሰነ መልክ ስለ ተቃራኒ ቡድን በሚዲያዎች ዕያየን ነበር እና ከእኛ በላይ ተደራጅተዋል ምንም ጥያቄ የለውም። 7/8 ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ይዘዋል እና የእኔ ተጫዋቾች ይህንን ሁሉ ነው ያሸነፉት። የአፍሪካ እግርኳስ ስለሚታወቅ ኳሱን ካፈጠንባቸው ቀዳዳዎችን እናገኛለን ብለን ከተጫዋቾች ጋር ተነጋግረናል። ያንን ነው የተገበሩት።”


አሰልጣኝ ርዋካ ክላውዲ – ራየን ስፖርትስ

“ቡድናችን አዲስ ነው። ከተመሠረተ ሁለት ዓመቱ ነው። በዚህ መድረክ መሳተፋችን በራሱ ትልቅ ስኬት ነው። ዛሬ ጨዋታው በጣም ጠንካራ ነበር። ተጋጣሚያችን ንግድ ባንክ ለመድረኩ ቤተሰብ የሆነ ጠንካራ ቡድን ነው። ጨዋታው ላይ ጥሩ ነበርን። አጀማመራችን ጥሩ ባይሆንም በኋላ ላይ ግን ተቀናጅተን ተጭነናቸው ነበር ነገር ግን ተሸንፈናል ፤ ያው እግርኳስ ነው። ቅያሪዎቻችን ጥሩ ነበሩ። 6 ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች አሉን ለአብነት ያህል ከማላዊ ፣ ከኬኒያ ፣ ከታንዛኒያ የመጡ አሉ። ከጨዋታ በፊት ስለተጋጣሚያችን ለማየት ብንሞክርም አዳጋች ነበር የተወሰነ ብናይም በቂ አልነበረም።”