የዋልያዎቹን ስብስብ ሰባት ተጫዋቾች አልተቀላቀሉም

በመጪዎቹ ቀናት ከፊታቸው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች የሚጠብቃቸው ዋልያዎቹ ሰባት ተጫዋቾች እስካሁን ስብስቡን አለመቀላቀላቸው ታውቋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2025 ሞሮኮ ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ስምንት ከጊኒ ታንዛኒያ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የተደለደለች ሲሆን ለዚህም ይረዳ ዘንድ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በትናትናው ዕለት በአዳማ ከተማ በመሰባሰብ ዝግጅታቸውን ዛሬ ጀምረዋል።

በዛሬው የመጀመሪያ ልምምድ ወቅት ጥሪ ከደረሳቸው ተጫዋቾች መካከል ፍሬው ጌታሁን፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ሲሌይማን ሀሚድ፣ ከንዓን ማርክነህ፣ አቤል ያለው፣ አቡበከር ናስር እና ሱራፌል ዳኛቸው ያልተገኙ ተጫዋቾች መሆናቸውን ለመታዘብ ችለናል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮቹ ፍሬው ጌታሁን፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ፈቱዲን ጀማል ክለባቸው ከትናት በስቲያ በነበረው ጨዋታ ምክንያት ዛሬ ወደ ሀገርቤት የሚመለሱ በመሆኑ ከነገ ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ሲጠበቅ የቀሩት ተጫዋቾች ያልተገኙበትን ምክንያት ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ሲሆን አሰልጣኝ ገብረመድህን በምትካቸው ሌሎች ተጫዋቾች ይተካሉ ወይስ ባለው ስብስብ ይቀጥላሉ የሚለውን ጉዳይ በቀጣይ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።

የቡድኑ የዛሬ ልምምድ ውሎን በተመለከተ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃ እየተከታተልን ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።