ዛሬ ዝግጅቱን በጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ካልነበሩት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሱራፌል ዳኛቸው መቼ ቡድኑን ይቀላቀላል ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋለች።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጥሪ ካደረጉላቸው 28 ተጫዋቾች መካከል ለአሜሪካው ክለብ ሎውዶን ዩናይትድ የሚጫወተው አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው አንዱ ነው ፤ በዛሬው የብሔራዊ ቡድኑ ልምምድ ላይ ያልተገኘው ሱራፌል ከብሔራዊ ቡድን ጥሪ አስቀድሞ ከሀገረ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አረጋግጠናል።
ታዲያ ሱራፌል መች ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላል በማለት ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ሱራፌል ከብሔራዊ ቡድን ጥሪ አስቀድሞ የስራ ቪዛ እንዲያጠናቀቅ ክለቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደላከው እና ሱራፌል ሀገር ቤት ከመጣ በኋላ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ እንደረሰው ሰምተናል።
ይህን ተከትሎ ክለቡ ሱራፌል ዳኛቸው ለብሔራዊ ቡድን መጠራቱን መረጃ የሌለው ሲሆን ፌዴሬሽኑ በኢሜይል ለክለቡ ሎውዶን ዩናይትድ እንዲያውቅ ካደረገ በኋላ በቀጣዮቹ ቀናት የዋልያዎችን ስብስብ እንደሚቀላቀል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።