አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ምክትሎቻቸውን አሳውቀዋል

አዳማ ከተማ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ቀጥሯል።

ከአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጋር ከተለያዩ በኋላ በቡድኑ ውስጥ በምክትል አሰልጣኝነት እና በቡድን መሪነት ሲያገለገል የቆዩትን አብዲ ቡሊን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት አዳማ ከተማዎች አሁን ደግሞ ሁለት ምክትል አሰልጣኞችን መቅጠራቸው ታውቋል።

ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት ከተቀላቀሉት አንዱ ብርሃኑ ቃሲም ነው። ረዘም ላሉ ዓመታት ለአዳማ ከተማ ከተጫወተ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ደግሞ ወደ የመን አቅንቶ መጫወት የቻለው የብሔራዊ ቡድን የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ወደ አሰልጣኝነት ሕይወት ከመጣ በኋላ በታዳጊ ቡድኖች እና በአዳማ ከተማ የሴቶች ቡድን በረዳት አሰልጣኝነት እና በዋና አሰልጣኝነት መሥራት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ወንዶቹ መጥቶ ምክትል አሰልጣኝ እንዲሆን በአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ተመርጧል።

ሌላኛው ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት የተቀላቀለው ሳሙኤል አበራ ነው። የአዳማ ከተማ ሴቶች ቡድን የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን ሲሆን በአሰልጣኝነት መምራት የቻለው አሰልጣኙ ላለፉት ሦስት ዓመታት በታዳጊ ተጫዋቾች አሰልጣኝነት በግሉ ሲሠራ ከቆየ በኋላ እንደ ብርሃኑ ቃሲም ሁሉ ወደ ዋናው የአዳማ ከተማ ቡድን አቅንቶ ምክትል አሰልጣኝ እንዲሆን ተወስኗል።

በተጨማሪም ክለቡ ገዛኸኝ ለማን በቡድን መሪነት መቅጠሩ የተሰማ ሲሆን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የሆነው መስፍን ነጋሽ ባለበት ኃላፊነት እንደሚቀጥል ታውቋል።