የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እንደማያገኙ ታውቋል።
ከነሐሴ 11 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 23 እንደሚቆይ መርሐግብር የወጣለት የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ውድድር ላለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ እና በአበበ ቢቂላ ስታዲየሞች አራት ጨዋታዎች ሲደረጉበት ትናንት 5 ሰዓት ላይ ሊደረግ ከነበረው እና በዝናብ ምክንያት ከ1 ሰዓት በላይ ዘግይቶ ከተጀመረው የፒቪፒ ቡዌንዚ እና ካዌምፔ ሙስሊም ጨዋታ ውጪ ሌሎቹ ሦስት ጨዋታዎች በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እያገኙ ቀጥለው ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ ባደረገችው ማጣራት ደግሞ ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እንደማይኖረው አረጋግጣለች።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እንዲያገኝ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር የገባው ስምምነት በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በኩል በምን ምክንያት እንደተቋረጠ ግልጽ ባይሆንም ፌዴሬሽኑ ውድድሩ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን የሚያገኝበትን አማራጭ እየፈለገ እንደሚገኝም ተሰምቷል።