በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሱዳኑን የይ ጆይንት ስታርስ 4ለ0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የተቀላቀለ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቅዳሜ ዕለት በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ራዮን ስፖርትን 3ለ2 ካሸነፉበት አሰላለፍ ግብ ጠባቂዋን ታሪኳ በርገናን እና የመሃል ተከላካይዋን አሳቤ ሙሶን አስወጥተው ግብ ጠባቂዋን ንግሥት እና መሠረት ወርቅነህን አስገብተዋል።
5 ሰዓት ሲል በሩዋንዳዊቷ የመሃል ዳኛ አሊኔ ኡሙቶኒ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ፍጹም ብልጫ መውሰድ ሲችሉ ገና በ30ኛው ሴኮንድ ነበር በሴናፍ ዋቁማ ጎል ጨዋታውን መምራት የጀመሩት። በመክፈቻው ጨዋታ በ20ኛው ሴኮንድ ጎል አስቆጥራ የነበረችው ሴናፍ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በ30ኛው ሴኮንዶ ጎል ማስቆጠሯ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ሆኗል።
በሚያገኟቸው ኳሶች ሁሉ በፈጣን ቅብብል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመጠጋት ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ባንኮቹ 9ኛው ደቂቃ ላይ በአረጋሽ ካልሳ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ራሷ አረጋሽ ከቅጣት ምት ወደ ጎል የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ናዋል አይዛክ ስትመልሰው ሳትዘጋጅ ያገኘቸው አዲስ ፈራሚዋ መሠረት ወርቅነህ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።
የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የተቸገሩት የይ ጆይንት ስፖርቶች 20ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። ግብ ጠባቂዋ ናዋል አይዛክ ሄንሪ ማጆክ በሴናፍ ዋቁማ ላይ በሠራችው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አማካይዋ እመቤት አዲሱ መረብ ላይ ስታሳርፈው ለፍጹም ቅጣት ምቱ መገኘት ምክንያት የነበረችው ሴናፍ ዋቁማም በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ደግሞ ሦስተኛውን ጎል ማስቆጠር ችላለች።
የቡድኑ አዲስ ፈራሚ የሆነችው የመስመር አጥቂዋ ንግሥት በቀለ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆና እንዲሁም አረጋሽ ካልሳ ከሴኮንዶች በኋላ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸውን ጠንካራ ሙከራዎች ግብ ጠባቂዋ ናዋል አይዛክ አግዳባቸዋለች።
የደቡብ ሱዳን ተወካይ ሆነው የመጡት የይ ጆይንት ስታርስ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት አጋጣሚ ልፋታቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ አራተኛ ጎል 37ኛ ደቂቃ ላይ ተቆጥሮባቸዋል። በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን ስታሻማው ኳሱን ያገኘችው ሌላኛዋ አዲስ ፈራሚ ታሪኳ ዴቢሶ በግንባር በመግጨት ኳሱን መረብ ላይ ማሳረፍ ስትችል 45ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አረጋሽ ካልሳ ከማቀበል አማራጭ ጋር ያገኘችውን ንጹህ የግብ ዕድል ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክናው ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከዕረፍት በፊት ለብሰውት የገቡትን ማልያ ከዕረፍት ሲመለሱ በሌላ ቀለም ማልያ ቀይረው ለብሰው የገቡበት አጋጣሚ ያልተለመደ ነበር።
ንግድ ባንኮች በርካታ የተጫዋች ቅያሪዎችን በማድረግ ጨዋታውን ሲያስቀጥሉ መሠረት ወርቅነህ ፣ ሲሣይ ገብረዋህድ ፣ መሳይ ተመስገን እና አረጋሽ ካልሳ ከረጅም ርቀት ያደረጓቸውን ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ግብ ጠባቂዋ ናዋል አይዛክ ሄንሪ ማጆክ አግዳቸዋለች። ጨዋታውም ከዕረፍት በፊት በተቆጠሩ ግቦች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የተቀላቀለ የመጀመሪያው ቡድን መሆኑን አረጋግጧል።