👉 “ከጨዋታ ጨዋታ እየተማርን ነው” አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው
👉 “በጨዋታው ብንሸነፍም ደስተኛ ነኝ” ምክትል አሰልጣኝ ሶኒ ሀሪየድ
በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሱዳኑን የይ ጆይንት ስታርስ 4ለ0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ከተቀላቀለ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለጋዜጠኞች የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ወደ ቀጣይ ዘር ስለ ማለፋቸው…?
“ይሄ ውድድር ከተጀመረ አራት ዓመታት አስቆጥሯል፤ አራቱንም ዓመታት ግማሽ ፍፃሜ ገብተናል። ቡድናችን ምን ያህል ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ዐይተናል። ዛሬም ውጤቱን ካገኘን በኋላ ማየት የምንፈልጋቸው በርካታ ተጫዋቾች ቀይረን በማስገባት ዐይተናል ይሄ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።”
ስለ አጨዋወታቸው…?
“ብዙ ጊዜ አሰልጣኝ ሜዳ ላይ ባለው እንቅስቃሴ አይረካም የሚጎድሉት ነገሮችን ስለምታይ፤ ከጨዋታ ጨዋታ እየተማርን ነው። ይሄ ፈትኖናል በቀጣይም ከዚህ በላይ የሚፈትነን ስለሚኖር እዛ ላይ እናስተካክላለን።”
በቡድኑ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ስሜት…?
“እስካሁን ድረስ ባለው ነገር ሦስቱንም ዓመታት ይለፋሉ ይጥራሉ፤ ሁለት ጊዜ ሁለተኛ አንድ ጊዜ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዘን ጨርሰናል ስለዚህ ቁጭት በውስጣቸው አለ። የባለፈውን ልምድ እንደ ትምህርት እንወስዳለን ተጫዋቾቼ ላይ ያለው ተነሳሽነት ግን የሚደነቅ ነው።”
ስለ ተጫዋቾቹ አሁናዊ ብቃት…?
“ባለፈው ዓመት ከነበሩ ተጫዋቾች ቢያንስ ስምንቱ እዚህ ቡድን ውስጥ የሉም፤ አሁን ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾች አካተናል። እግር ኳስ ነው ትዕግስት ይፈልጋል፤ ነገሮች በአንዴ አይስተካከሉም።
የምንፈልገው ደረጃ ላይ አለን ለሚለው ጥያቄ በሂደት የሚታይ ይሆናል፤ ማስተካከል ያለብን ግን እናስተካክላለን። ሌላ ተጨማሪ ውድድር እና የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች የሚፈልጉ ተጫዋቾችም ይኖራሉ። በሁለቱም ጨዋታዎች ዕድል ሰጥተናል አንድ የተውጣጣ ጠንካራ ቡድን እንሠራለን።”
ምክትል አሰልጣኝ ሶኒ ሀሪየድ – የይ ጆይንት ስታርስ
“በጨዋታው ብንሸነፍም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ እስካሁን ተስፋ አልቆረጥንም። ተጋጣሚያችን አንድ ደቂቃ ሳይሞላ ጎል ቢያስቆጥርም ወደ ጨዋታው እንመለሳለን ብዬ አስቤ ነበር። ተጫዋቾቼ የቻሉትን ሁሉ ሞክረዋል ግን ያው እግርኳስ ነው። የንግድ ባንክ ተጫዋቾች ልምድ አላቸው፤ አብዛኞቹ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ብዙ አለምዓቀፍ ጨዋታዎች አከናውነዋል። በወጣቶች የተሞላ ቡድን እንደመያዛችን የእነሱ ደረጃ ላይ እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለኝ ተጫዋቾቼንም አበረታትቻዋለሁ። ምክንያቱም ከንግድ ባንክ ጋር በቅንጅትም ይሁን በእንቅስቃሴ ትልቅ ልዩነት አለን።”