ማሊያዊው ግብ ጠባቂ ወደ አዲስ ክለብ አምርቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባት የውድድር ዓመታትን ያሳለፈው የግብ ዘብ ወደ ሌላኛው የሀገራችን ክለብ ማምራቱ ዕውን ሆኗል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሠ መሪነት ለ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፏቸው በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሠሩ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች የቃለአብ ውብሸት ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ መለሠ ሚሻሞ እና ሳሙኤል ዮሐንሰን ውል አራዝመው ኢዮብ ዓለማየሁ ፣ በረከት ወንድሙ ፣ ጫላ ተሺታ እና ብሩክ በየነን የግላቸው ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ማሊያዊውን የ32 ዓመት ግብ ጠባቂ ሳማኪ ሚካኤልን የስብሰባቸው አካል አድርገዋል።

የሀገሩን ክለብ ዱጉ ወለፊያን በመልቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ከፋሲል ከነማ ጋር ላለፉት ሰባት ዓመታት ግልጋሎት የሰጠውን እና በክረምቱ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ከረጅም ዓመታት በኋላ ከክለቡ ጋር የተለያየው የግብ ዘቡ ቀጣዩ መዳረሻው ሀድያ ሆሳዕና መሆኑን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።