👉 “እጅግ እየተሳካለት ከመጣ ድርጅት ጋር ትስስር መፍጠራችን ያስደስተናል።” አቶ ነዋይ በየነ
👉 “ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚመጥን መልኩ ጥራት ያላቸውን ትጥቆች በማቅረባችን ኩራት ይሰማናል።” አቶ ሳሙኤል መኮንን
ዛሬ አመሻሽ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በጎፈሬ መካከል ለሁለት ዓመት የሚቆይ እንደ ሁኔታው ዕየታዬ የሚሻሻል የትጥቅ አቅርቦት የፊርማ ስነ ሥርዓት በቤስት ዌስተርን ፕላስ ፐርል አዲስ ሆቴል መካሄዱ ይታወሳል።
በስምምነቱ ወቅት አስቀድመው የመግቢያ ንግግር ያደረጉት አቶ ነዋይ በየነ “ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ከጎፈሬ ጋር አብሮ ለመሥራት እንዳሰቡ እና ጎፈሬ “ከሚጠብቁት በላይ በፍጥነት ዕያደገ፣ እጅግ እየተሳካለት ከመጣ ድርጅት ጋር ትስስር መፍጠራችን ኩራት ይሰማናል ፤ ያስደስተናል።” ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጎፈሬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረገው ስምምነት ሌሎች ክለቦች እንደነዚህ ያሉ አገልግሎቶች እንዲሰጥ እንደሚያስችለው በመግለፅ “ጎፈሬ ከኢትዮጵያ ውጭ አድማሱን በማስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆንን እናውቃለን እኛም የዚህ ተቋም ቤተሰብ በመሆናችን ደስተኛ ነን ካሉ በኋላ በመጨረሻም “ጎፈሬ ይሄን ዕድል ስለሰጠን ከእኛ ጋር አብሮ በመሥራቱ ደስተኛ ነን” ብለው ስምምነቱ የቢዝነስ መልክ ያለው የድጋፍ ወይም የዕርዳታ ስምምነት የተወ የጋራ ጥቅምን ያማከለ ግንኙነት መመስረቱን በሚቀርበው ትጥቅ ጥራት ጥያቄ እንደሌላቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በሚኖራቸው ቆይታ ዓመቱ የተሳካ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
በማስከተል የተናገሩት የጎፈሬ መስራች አቶ ሳሙኤል መኮንን “ቀደም ባሉ ዓመታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ እና ዛሬ ደግሞ ጎፈሬ አድጎ እና ጎርምሶ ሙሉ ለቡድኑ አባላት በውጭ የሚገኙትን ምርቶችን አሟልቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚመጥን መልኩ ጥራት ያላቸውን ትጥቆች በማቅረባችን ኩራት ይሰማናል።” በማለት ተናግረው “ጎፈሬ ከሀገር ወጥቶ በምስራቅ አፍሪካ ታዋቂ ብራንድ ሆኗል። ይህ ለኢትዮጵያ ኩራት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰማንያ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ኩራት የሆነ ክለብ ነው ከኢትዮጵያ ውጭ ስንወጣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አትሰሩም ወይ በማለት ይጠይቁን ነበር። ዛሬ ይህን መልስ በመስጠታችን በጣም ደስ ብሎናል።” ብለዋል።
በመቀጠል በቦታው ከተገኙ የሚዲያ አካላት ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ ዳዊት ውብሸት ምላሽ ሰጥተዋል።
“ጎፈሬ ዛሬ አይደለም ከእኛ ጋር መሥራት የጀመረው። አራት አምሥት ዓመት ይሆናል የጀመሩትም የደጋፊዎችን ማልያ በመሥራት ነበር። እንደሚታወቀው እኛ ከማክሮን ጋር ውል ገብተን ከጣልያን ሀገር ነበር ትጥቆቻችንን የምናስመጣው። ሆኖም ግን ሀገሪቷ ውስጥ በነበረው የዶላር እጥረት ከዛም ደግሞ ታክስ እየጨመረ በመምጣቱ እንጂ ዕቃዎችን እናመጣ ነበር። ምክንያቱም ማክሮን በጣም ትልቅ ኩባንያ እንደመሆኑ እና ለሌሎች ትልልቅ ክለቦች የሚያመርቱ ስለሆነ ወደ እኛ ሲመጣ መዘግየቶች እየተፈጠሩ ስለመጡ እና የዶላር ዕጥረት ስለተከሰተ እንዲሁም ታክስ ላይም አላስፈላጊ መስዋዕቶችን እየከፈልን ስለሆነ ሀገር በቀል ኩባንያ በመምጣቱ ይሄን ነገር እንዲያስቀርልን ሁልጊዜ እየተመካከርን ነበር። ከሦስት ኩባንያዎች ጋር አብረን እንሠራ ነበር ፤ ግን ላለፉት ሦስት ዓመታት ዋናው ቡድን ሲጫወት የጎፈሬን ማልያ ብቻ ነበር የሚያደርገው። በልምምድ እና በሌሎች አጋጣሚዎች ግን ሌሎችን ማልያዎች እንጠቀም ነበር ምክንያቱም ሁሉንም ማመዛዘን ስለነበረብን ማለት ነው። ነገር ግን ጎፈሬ ከጥራቱም ሆነ ከተደራሽነቱ አኳያ መጋዝናቸው ፋብሪካቸው ድረስ ሄደን ጎብኝተን ያላቸውን ነገሮች በማየት ጎፈሬ ብልጫ ወስዶ ስለተገኘ ያው ለዛ ነው ያስገባነው። ከብር አኳያ ይሄ ኮንትራት የሚፈረመው እና እንደ ሁኔታው እየታየ የሚቀጥል ሆኖ ለሁለት ዓመት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ቡድኖች አሉት ዋናው ቡድን ፣ ሴቶች ቡድን ፣ ከ17 እና ከ20 በታች ቡድኖች አሉ ከዚህ በተጨማሪ የክብደት ማንሳት ቡድንም አለን። አጠቃላይ ለሁሉም የስፖርት ውድድሮች በሚወጣበት ጊዜ ዋና ማልያ ፣ መለማመጃ ፣ ለጉዞ የሚሆኑትንም ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ ትጥቆችን ያቀርቡልናል ማለት ነው። በማለት በተመን ደረጃ ወደ ሃያ ሚሊየን ብር የሚፈጅ ስምምነት እንደሆነም አብራርተዋል። አቶ ዳዊት በመጨረሻም ከዊን አቋማሪ ድርጅት ጋር የነበራቸው ውል እንደተቋረጠ እና ከፀሐይ ባንክ ጋር ያለውን ውል በተመለከት እየተነጋገሩ ስለሆነ አሁን ላይ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
አቶ ሳሙኤል መኮንን ሌሎች ‘ብራንዶች’ ተቀላቅለው ስለ ሚለበሱበት ሂደት ለተነሳባቸው ጥያቄ ሲመልሱ…
“ጎፈሬ እንደ ፈር ቀዳጅነቱ የስፖርት ትጥቅ እውቀቱን ከፍ እያደረግን ለማምጣት አስበናል። አንደኛው ሂደት የነበረው የ’ብራንድ’ አስተሳሰብ አንድ ክለብ ከአንድ ትጥቅ አቅራቢ ጋር ሲዋዋል የሌላን አለመጠቀም ነው፤ እዚህ አንድ ትልቅ ማነቆ ሆኖብን የነበረው የጨረታ አስተሳሰብ ነው። ጨረታ እና የትጥቅ አቅርቦት በጣም የሚጋጩ ነገሮች ናቸው። የተቋማት ክለቦች ሁሉም ጨረታ አውጥተው ነው ግዢ የሚፈፅሙት፤ ጎፈሬ ካሳካቸው ነገሮች አንዱ የግዢ ስርዓቱን ማስተካከል ነው። ፈርቀዳጅነት ማለት ያንን አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠር አድርገናል ብለን እናስባለን፤ ግን የሚቀረን ነገር አለ። ቅድም እኛን የሚመስሉ ክለቦች ያልኩት ይሄንን ነው። እንደ ፈር ቀዳጅነታችን አሰራሩን እያሰረፅን ነው፤ አሁን ደግሞ ሂደቱ የጎለበተበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ሂደት የመጣ ክለብ ነው ከትላልቅ የውጪ ተቋማት ጋር ሲሠራ ቆይቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዛሬ ጀምሮ ከጎፈሬ ጋር ይሠራል ይሄንን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን የሚገኙ ትላልቅ ክለቦች አድርገውታል። ከአስተሳሰብ ጋር ተያይዞ በመጡ ችግሮች ነው አንዱ ከአንዱ ቀላቅሎ የመጠቀም ክፍተት የመጣው።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።