በትናንትናው ዕለት በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በርካታ ተጫዋቾችን ለማስፈረም መስማማታቸው ታውቋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ23 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ ለከርሞው የሊጉ ተሳታፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት ወልቂጤ ከተማዎች ለአዲሱ የውድድር ዘመን የቀድሞውን ፌዴራል ዳኛ ሶሬሳ ካሚልን በዋና አሰልጣኝነት ከሳምንታት በፊት መሾማቸው ይታወቃል።
የክለብ ላይሰንሲንግን ወሳኝ መስፈርቶች ባለማሟላታቸው ተጫዋች ማስፈረም እንዳይችሉ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዕገዳ የተጣለባቸው ወልቂጤዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ከዛሬ አንስቶ በሀዋሳ ከተማ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ቡድኑም ራሱን ለማጠናከር አስራ አንድ የሚደርሱ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ተስማምተዋል።
የቡድኑ ቀዳሚው የዝውውር ስምምነት አጥቂውን ሔኖክ አየለን ወደ ቀደመ ክለቡ የመለሰ ሆኗል ፤ ከዚህ ቀደም በደቡብ ፓሊስ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና የተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደግሞ በደብረብርሃን ከተማ ያሳለፈው አንጋፋው አጥቂ ወደ ቀድሞ ቡድኑ አምርቷል።
ሌላኛው ባለ ልምዱ ቢያድግልኝ ኤልያስ ነው ፤ በአርባምንጭ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ወልዲያ እና ደብረብርሃን ከተማ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ሠራተኞቹን ለመቀላቀል ተስማምቷል።
የቡድኑ ሶስተኛ ለመፈረም የተስማማው በቀኝ ተከላካይ ስፍራ ለአዲስ አበባ ከተማ ፣ ድሬዳዋ እና ያለፉትን ሦስት የውድድር ዘመናት በሀምበርቾ ያሳለፈው ምንያምር ጴጥሮስ ነው።
በተጨማሪነትም ከሀዋሳ ታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ድረስ ለተከታታይ አራት ዓመታት ያገለገለው ወጣቱ አጥቂ ሀብታሙ መኮንን ፣ ከሀዋሳ ወጣት ቡድን እስከ ዋናው ድረስ እንዲሁም ደግሞ በደደቢት ፣ ወልዋሎ እና ሲዳማ ቡና ፣ ሀምበርቾ መጫወት የቻለው የተከላካይ አማካዩ ብርሀኑ አሻሞ ፤ በአማካይ ስፍራ ላይ ለሀዋሳ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ዓምና በሻሸመኔ ከተማ ቆይታ የነበረው ሔኖክ ድልቢ ፤ ለወላይታ ድቻ ፣ ቦዲቲ እና ያለፈውን የውድድር ዘመን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዝናቡ ዳመነ ፤ በሀዋሳ ወጣት ቡድን በመቀጠል ለደቡብ ፓሊስ ፣ ነገሌ አርሲ እና ደሴ የተጫወተው ወጣቱ ተከላካይ ፍፁም ተስፋዬ ፤ በሸገር ከተማ በአጥቂነት የተጫወተው ሀይከን ድዋሙ ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጣት ቡድን የነበረው አጥቂው ብሩክ ነጋሽ እና በአዲስ ከተማ ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ጌታሁን አማረ የወልቂጤ ተጫዋች ለመሆን የተስማሙ መሆናቸው ተረጋግጧል።