አዳማ ከተማ ሁለት ግብ ጠባቂዎች ወደ ስብስቡ አካትቷል

በባቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ሁለት የግብ ዘብ አስፈርመዋል።

በዋና አሰልጣኙ አብዲ ቡሊ እና ረዳቶቻቸው በባቱ (ዝዋይ) ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየከወኑ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ለቀጣዩ የ2017 የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ተጠናክረው ለመቅረብ እንደ ስንታየሁ መንግሥቱ እንዲሁም ደግሞ የቀድሞ ተጫዋቾቻቸውን አቡበከር ወንድሙ እና አሜ መሐመድን ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉ ሲሆን አሁን ላይ ሁለት ግብ ጠባቂዎችንም ወደ ቡድናቸው አካትተዋል።

ቡድኑን የተቀላቀለው ቀዳሚ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ ነው። ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተገኘ በኋላ ለሀዋሳ ከተማ ወጣት ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ሲሆን በቀድሞው አጠራሩ ለዲላ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ እንዲሁም ወደ ሀዋሳ ከተማ በመመለስ ዋናውን ቡድን አገልግሎ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት ደግሞ በመቻል ቆይታን ካደረገ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻው አዳማ ከተማ ሆኗል።

ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመም ወደ ቀድሞው ክለቡ ተመልሷል። የቀድሞው የሀምበርቾ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ደግሞ በአዳማ ከተማ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን ዳግም ከተመለሰበት አዲስ አበባ ከተማ በኋላ በድሬዳዋ ከተማ ሁለት የውድድር ዓመታትን ቆይቶ በድጋሚ ወደ ቀደመው ክለቡ አዳማ የሚመልሰውን ዝውውር አገባዷል።