በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የቀድሞ ግብ ጠባቂያቸውን ሲያስፈርሙ ከተካላካዩ ጋር ተለያይተዋል።
የቀድሞ ተጫዋቾቻቸውን እና በአሰልጣኝነትም ጭምር ክለቡን ማገልገል የቻለውን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ዳግም ወደ ስብስባቸው ያካተቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን እነርሱን ለመተካትም ፍፁም ጥላሁን ፣ ፀጋ ከድር እና ፓውሎስ ከንቲባን ወደ ስብስባቸው ሲቀላቅሉ ቶሎሳ ንጉሤን ለማስፈረም ደግሞ በቃል ደረጃ ስምምነት መፈፀማቸው ይታወሳል።
በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ክለቡ የቀድሞ ግብ ጠባቂውን ተመስገን ዮሐንስን በድጋሚ አስፈርሟል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ግልጋሎት የሰጠው ወጣቱ የግብ ዘብ ከኢትዮጵያ መድን የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በስምምነት በመለያየት ወደ ቀደመ ክለቡ ተመልሷል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ከቀናቶች በፊት ለክለቡ ፊርማውን ያኖረው የክለቡ የቀድሞ ተከላካይ እንዲሁም በመቀጠል ለጅማ አባጅፋር ፣ መቻል እና ያለፈውን ዓመት በሻሸመኔ የነበረው የአብሥራ ሙሉጌታ ከክለቡ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች እንደማይቀጥል ተሰምቷል።