ትውልደ ኢትዮጵያዊው ወደ ባየርን ሚዩኒክ ሁለተኛ ቡድን አድጓል።
ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በጀርመኑ ታላቅ ክለብ ባየርን ሚዩኒክ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በታች ቡድን በመጫወት ላይ የቆየው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አማካይ ልዑል ብሩክ ዓለሙ ወደ ሁለተኛው ቡድን አድጓል። ወደ ባቫርያኖቹ ከመቀላቀሉ በፊት የእግር ኳስ ሕይወቱ በጀመረበት የበርሊኑ ‘Hertha 03 Zehlendorf’ ጨምሮ ‘Hertha BSC’ እና ‘FC Viktoria 1889 Berlin’ በተባሉ የታዳጊ ቡድኖች ቆይታ ካደረገ በኋላ በ2018 ታላቁን ባየርን ሚዩኒክ ተቀላቅሎ በቡድኑ ሦስት የዕድሜ እርከኖች ተጫውቶ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየው ይህ የአስራ ዘጠኝ ዓመት ተጫዋች በ’Regionalliga bayern’ የሚሳተፈውን የዋናው ቡድን መጋቢ የሆነው ባየርን ሚዩኒክ ሁለት ተቀላቅሏል።
ባለፈው ዓመት ‘ torn cruciate ligament ‘ ጉዳት ገጥሞት በርከት ላሉ ወራት ከሜዳ ለመራቅ ተገዶ የነበረው ይህ ተጫዋች ከባየርን ሚዩኒክ ጋር እስከ 2025 የሚያቆየው ውል ያለው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በቅርቡ በተጀመረው Regionalliga bayern በመሳተፍ ላይ ይገኛል። በወጣቱ አሰልጣኝ ሆልገር ሴይትዝ የሚሰለጥነው እና በባየርን ሚዩኒክ እግር ኳስ ክለብ የወጣት ቡድኖች አደረጃጀት ውስጥ የመጨረሻው እርከን ላይ ያለው ይህ ቡድን ከአስራ ስምንት እስከ ሃያ ሦስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾችን ያቀፈ ሲሆን ዋና ዓላማውም ወጣቶችን ለዋናው ቡድን ማብቃት ነው።