የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኬኒያ ፖሊስ ቡሌትን 2ለ1 በመርታት ሲያሸንፍ ሁለቱም ተያይዘው ከምድቡ አልፈዋል።
በምድብ አንድ የተደለደሉት እና አንደኛ እና ሁለተኛ ላይ ተቀምጠው የሚገኙትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኬኒያውን ፓሊስ ቡሌት ባገናኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በጣለው ዝዛብ ምቹ ባልሆነው ሜዳ ላይ ተከናውኗል። ጨዋታውን ከፍ ባለ የሽግግር አጨዋወት የጀመሩት ንግድ ባንኮች 3ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ከመሐል ወደ ወደ ግራ በአግባቡ ያቀበለቻትን ኳስ አረጋሽ ካልካ ነፃ ቦታ ለነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ስትሰጣት አጥቂዋ ኳስን ከመረብ አዋህዳ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጋለች።
ኳስን በምቹነት ለማንሸራሸር በእጅጉ ምቹ ባልነበረው ሜዳ ንግድ ባንኮች በመስመሮች በኩል በይበልጥ ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ በተሻጋሪ እና በጥልቅ አጨዋወት መጫወትን የመረጡት ኬኒያ ፓሊሶች ወደ ጨዋታ በመግባት ጫና ሲፈጥሩ ታይተዋል። ከግራ በኩል ንግስት በጥሩ የእግር ስራ ለሴናፍ ሰጥታት ካመከነችው ከሦስት ደቂቃዎች መልስ ፓሊሶች በአኪኒ ኦክዋሮ አደገኛ ሙከራን አድርገው የግብ ዘቧ ታሪኳ በርገና በሚገርም ብቃት ከግብነት ኳሷን አግዳባታለች።
20ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች ፈጠን ብለው ለማጥቃት በሄዱበት የቀኝ የሜዳው ክፍል ንግስት ወደ ግራ አዘንብላ ላለችው አረጋሽ ሰጥታት ከሴናፍ ጋር ተቀብላ ሞክራ ግብ ጠባቂዋ ኩንዱ ኩዋማሲ መክታባታለች። ኳስን በሚይዙበት ወቅት በተሻለ ፈጣን ሽግግሮች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ጫናን በማሳደር ብልጫን መያዝ የቻሉት ኬኒያ ቡሌት ፓሊሶች 33ኛው ደቂቃ ከእጅ ውርወራ የደረሳት ኳስ ሊዲያ አኮቴ አሻምታ በተደጋጋሚ ጥሩ እንቅስቃሴን ስታደርግ የነበረችው አኪኒ ኦኮዋሮ በግንባር ገጭታ ታሪኳ መረብ ላይ አስቀምጣ ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል።
ተመጣጣኝ የሚመስል ነገር ግን ኬኒያ ፓሊሶች በተሻለ የማጥቃት ቅርፅ ለመጫወት በታተሩበት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃዎች ቡድኑ በድግግሞሽ ጫና ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበትን መንገድ ብንመለከትም የመጨረሻው የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ግን ወጥነት አልነበረውም። መጠነኛ መቀዛቀዞችን በእንቅስቃሴዎቻችን ያስመለከቱን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተለመደው የኮሪደር አጨዋወት በሚሄዱበት ወቅት ግን ያገኙትን ኳስ ከጎል አቆራኝተዋል።
59ኛው ደቂቃ ላይ ንግስት በቀለ ወደ ግራ ከሰናይት ቦጋለ የደረሳትን ኳስ ለልማደኛዋ ሴናፍ ስትሰጣት በቀላሉ የቡድኑን መሪነት ወደ 2ለ1 አሸጋግራለች። ከፉክክር አንፃር ወረድ ያሉ እንቅስቃሴን ያዘለ ከሙከራዎችን በተገደበ መልኩ የቀጠለው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምድቡን በበላይነት ሲፈፅም የኬኒያ ፓሊስን ሁለተኛ በመሆን ከምድብ ተያይዘው አልፈዋል።