ዝግጅቱን ከጀመረ አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብን አንድ ተጫዋች ተቀላቅሏል።
በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከታንዛኒያ፣ ጊኒ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዚህ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ከነሐሴ 13 ጀምሮ መቀመጫውን አዳማ ከተማ በማድረግ በወንጂ ሜዳ ልምምዱን በቀን ሁለት ጊዜ እየከወነ ይገኛል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋች መካከል አንዱ የሆነው ከንዓን ማርክነህ በግል ጉዳይ ምክንያት አሜሪካ ይገኝ ስለነበር እስከትላንት ቡድኑን ባይቀላቀልም ትናንት ማምሻውን ግን ቆይታውን አጠናቆ ወደ ሀገር ቤት መመለሱን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ በወንጂ ሜዳ ልምምድ መስራቱን ሰምተናል።
በሌላ ዜና ሱራፊል ዳኛቸው እስካሁን ብሔራዊ ቡድኑን ያልተቀላቀለ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚቀላቀል ሲሰማ የንግድ ባንኮቹ ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ፈቱዲን ጀማል ክለባቸው ነገ ከሚያደርገው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ በኋላ እሁድ ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አቡበከር ናስር እና አቤል ያለውን በተመለከተ ያገኘነውን አዳዲስ መረጃ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።