በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኤሴ ሲ ቪላ ጋር 1ለ1 ተለያይቶ በድምር ውጤት 3ለ2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።
በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ በመጀመሪያው ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀው የንግድ ባንክ እና የኤስ ሲ ቪላ ጨዋታ መልስ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በግብጻውያን ዳኞች እየተመራ ሲደረግ ጨዋታው እንደ ዐየር ንብረቱ ሁሉ ቀዝቃዛ ሆኖ ተስተውሏል።
መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ በቪላዎች በኩል ኤልቪስ ንጎንዴ 4ኛ ደቂቃ ላይ በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ፉዓድ ፈረጃ 8ኛ ደቂቃ ላይ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ 11ኛው ደቂቃ ላይ ቪላዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አንድሪው ኦቲም ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡ የላይ አግዳሚ መልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳይደረጉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል ንግድ ባንኮች 55ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ኪቲካ ጅማ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አዲስ ግደይ በግራ መስመር እየገፋ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ያገኘው ሳይመን ፒተር ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
በአንጻራዊነት ለተመልካች ሳቢ በነበሩት የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ንግድ ባንኮች 64ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፉዓድ ፈረጃ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሱሌይማን ሀሚድ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ጨዋታውን መምራት በጀመሩበት ቅጽበት በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት ባንኮች 72ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ቅብብል ወደ ሳጥን ያስገቡትን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው አግዶበታል።
በጥቂት ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት የመልስ ምት ለመስጠት ሲታትሩ የነበሩት ቪላዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ወደ አቻነት ተመልሰዋል። አይዛክ ካጁቢ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ ፈቱዲን ጀማል ጥፋት በመሥራቱ የተሠጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፓትሪክ ካካንዴ በአግባቡ አስቆጥሮታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድምር ውጤት 3ለ2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።