የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 – 1 ኤሴ ሲ ቪላ

👉 “ስጋት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ስጋት ላይ ነው ያለነው”

👉 “ፌደሬሽኑም ሊግ ካምፓኒውም ከጎናችን ይሆናል ብለን እንጠብቃለን”

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኤሴ ሲ ቪላ ጋር 1ለ1 ተለያይቶ በድምር ውጤት 3ለ2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ካለፈ በኋላ ቡድናቸውን በቴክኒካል ቦታ ቆመው ያልመሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው መጥፎ አልነበረም፤ ከሜዳችን ውጭ የነበረውን ጨዋታ አሸንፈው ሁለት ዕድል ይዘን ነው የገባነው ያንን ማስጠበቅ ይጠበቅብናል። ጎል አስቆጥረን የፍፁም ቅጣት ምት ከተቆጠረብን በኋላ ደግሞ ውጤቱን ወደ ማስጠበቁ መግባታችን እንድንቀዛቀዝ አድርጎናል። እንደነዚ ዓይነት ጨዋታዎች በጥንቃቄ የምትጫወታቸው ስለሆኑ ጥሩ ጨዋታ ነው ብዬ ነው የማስበው።

ስለ ቡድናቸው ሁኔታ

በጥራት ደረጃ ሜዳ ላይ ያየነው ጥሩ ነው። ምናልባት ያላስተዋላችሁት ነገር ግን አለ፤ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ያሉት ተጫዋቾቻችና ቁጥሩን ካየነው ስድስት ናቸው ከስድስቱም ሁለቱ ታዳጊዎች ናቸው፤ ከሦስቱ ተጫዋቾችም ሁለቱ ተመሳሳይ ቦታ የሚጫወቱ ናቸው። የቡድን ጥልቀት ላይ ከፍተኛ ጥያቄ ምልክት ነው ያለን። ከበጀት ወሰኑ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ነው ያለን። ስጋት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ስጋት ላይ ነው ያለነው። የቡድናችን ጥልቀት ጥያቄ ምልክት ነው ያለው።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች ?

በእንደዚ ዓይነት ውድድሮች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ብቻ አይደለም ወክለህ የምትጫወተው ሀገርን ወክለህ ነው። ፌደሬሽኑም ሊግ ካምፓኒውም ከጎናችን ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፤ በተለይም በዚ በተጫዋቾች ጉዳይ ስጋት ውስጥ ስላለን ሌላም የሀገር ጉዳይ ስለሆነም። ተጠባባቂ ወንበር ላይ ስድስት ተጫዋቾች ብቻ ተቀምጠው እንዴት ስድስት ብቻ ብለው ይጠይቁን ነበር። በቀጣይ እሱን ማስተካከል ትልቁ የቤት ስራችን ይሆናል።

በሁለቱም ጨዋታዎች የነበረው ልዩነት ?

መጀመርያ ሜዳው ተቀይሯል፤ እዛ ተመችቶን ነበር። ዛሬ ግማሹን አልተጫወትንም እንደሚታወቀው አበበ ቢቂላ ስቴድየም ትንሽ ይከብዳል፤ ዝም ብለህ ዘለህ የምትጫወትበት አይደለም ልምድ፣ ጉልበት፣ ጨዋታውን በአግብባቡ መቆጣጠር ይፈልጋል፤ ቅብብልህ የተሳካ መሆን ይገባዋል። ከዚ በተጨማሪም የመጀመርያው ጨዋታ ተፅዕኖም በዛሬው ጨዋታ ተፀዕኖ አለው። እሱን እያሰብክ ስለምትጫወት አቻ፣ ጎል ሳታስቆጥር መውጣት እና ማሸነፍ ብዙ አማራጭ ይዘህ ስለምትገባ የበለጠ ጨዋታው የመቆጣጠር እና ነጥብ ይዘህ መውጣት ጉዳይ ስለሆነ ዛሬ ከመጀመርያው ጨዋታ አንፃር በግማሽ ተቀዛቅዘናል።