👉 “የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር በድጋሚ የማሸነፍ ዕቅድ አለኝ”
👉 ” ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሀሩን ኢብራሂም ብዙ ነገር አግዞኛል”
የባለፈው የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል።
ከሀዋሳ ከተማ ጋር የተሳካ የውድድር ዓመት በማሳለፍ የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ዓመቱን ያገባደደው ኤርትራዊው ዓሊ ሱሌይማን ላለፉት ወራት ወደ ስዊድን አቅንቶ በዋናው ሊግ ተሳታፊ በሆነው ‘Gais’ የአጭር ጊዜ ቆይታ ካደረገ በኋላ በትናንትናው ዕለት ወደ አዲስ አበባ ገብቷል። ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ከአንድ ወር በላይ በነበረው ቆይታ የተሳካ ጊዜ ቢያሳልፍም ዝውውሩ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት ባለመሳካቱ ወደ ሀዋሳ ከተማ ተመልሶ ለመጫወት ኢትዮጵያ ገብቷል።
በዝውውሩ ሂደት ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ በስዊድን የተሳካ ጊዜ ማሳለፉን ገልጾ ዝውውሩ ባለመሳካቱ ውሉን አክብሮ በቀጣይ የውድድር ዓመት በሀዋሳ ከተማ ለመጫወት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ተናግሯል። “ቆይታዬ የተሳካ ነበር፤ በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች አስቆጥርያለሁ። እንቅስቃሴዬም ጥሩ ነበር፤ ግን ዝውውሩ ክለቡ ባቀረበልኝ ነገር እና በሌሎች አንዳንድ ነገሮች ሊሳካ አልቻለም” በማለት ተጨማሪ የውጭ ዕድሎች እንደነበሩትም ገልጿል። ” ከ ‘Gais’ በተጨማሪ ‘Göteborg’ እና ‘Värnamo’ የተባሉ እዛው ስዊድን የሚገኙ ክለቦችም ፈልገውኝ ነበር ግን የሀገሪቱ የዝውውር መስኮት ሊዘጋ ሁለት ቀናት ብቻ ስለቀሩት ሌሎች አማራጮ ለማየት በቂ ጊዜ አልነበረኝም፤ ግን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያለኝ ውል ካበቃ በኋላ በድጋሜ ተመልሼ ወደ ‘Gais’ ስለምቀላቀልበት ሁኔታ ከክለቡ ቴክኒካል ዳይሬክተር ‘Magnus Sköldmark’ ጋር ውጤታማ ንግግር አድርጌ ነው የተመለስኩት” ብሏል። ተጫዋቹ አክሎም የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ጥሩ እገዛ እንዳደረገለት በመግለፅ በክለቡ የአጭር ጊዜ ቆይታው የቋንቋ ችግሩን ለመፍታት እገዛ ላደረገለት ትውልደ ኢትዮጵያዊው የክለቡ ተጫዋች ሀሩን ኢብራሂም ምስጋናውን አቅርቧል።
በመጨረሻም በቀጣይ የውድድር ዓመትም በተመሳሳይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የተሳካ ዓመት አሳልፎ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር በድጋሚ ለማሸነፍ እቅድ እንዳለው በመግለፅ በቀጣይ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምር ገልጿል።