ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፍፃሜ ለማለፍ ወሳኙን ጨዋታ ነገ ያደርጋል

👉 ባንክ በወሩ 20ኛ ቀን 20ኛ የውድድሩ ጨዋታውን ነገ ያደርጋል
👉 የጨዋታ ሰዓቱ ቀድሞ ከተያዘለት መርሐ-ግብር ለውጥ ተደርጎበታል
👉 ደጋፊዎች በነቂስ ወተው ቡድኑን እንዲያበረታቱ ጥሪ ቀርቧል
👉 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቡድኑን አበረታቷል

የሴካፋ ዞን የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር በሀገራችን ኢትዮጵያ ከነሐሴ 11 ጀምሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። የምድብ ጨዋታዎችን አጠናቆ በነገው ዕለት በግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያዎች ወደ ወሳኝ ምዕራፎች የሚሸጋገረው ውድድሩ የፊታችን ሀሙስ የዞኑን ሻምፒዮን እንዲሁም የዋናው ውድድር ተሳታፊ ክለብ የሚለይ ይሆናል።

የ2016 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኬኒያ ፖሊስ፣ ዬ ጆይንት ስታርስ እና ራዮን ስፖርትስ ጋር በምድብ 1 ተደልድሎ የነበረ ሲሆን 9 ግቦችን በሦስት ጨዋታዎች በማስቆጠር በተቃራኒው ሦስት ተቆጥረውበት በ9 ነጥቦች ምድቡን በአንደኝነት አጠናቋል። በምድብ ሁለት ከሲምባ ኩዊንስ፣ ፒ ቪ ፒ እና ኤፍ ኤ ዲ ጂቡቲ ጋር ተደልድሎ 12 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ አስቆጥሮ በተቃራኒው 3 ገብቶበት በ6 ነጥቦች ምድቡን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ደግሞ የነገ የንግድ ባንክ ተጋጣሚ ነው።

በሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር 20ኛ ጨዋታቸውን ነገ የሚያደርጉት ንግድ ባንኮች በውድድሩ ታሪክ 15 ጨዋታዎችን አሸንፈው በሦስቱ ተሸንፈው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።

በጣም ደስተኛ መሆናቸውን የሚገልፁት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አራት ዓመታት ባስቆጠረው የውድድር መድረክ አራቱም ላይ በመሳተፍ ብቸኛ የሆኑ ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት በሁለቱ የፍፃሜ ተፋላሚ ሆነው ያለሙትን ዋንጫ ሳያገኙ ቀርተዋል። ዘንድሮ ለዚህ ዋንጫ እየተንደረደረ የሚገኘው ቡድኑ የደጋፊዎችን እገዛ እንደሚፈልግ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በተከታዩ ሀሳባቸው ይገልፃሉ።

“በውድድሩ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ አምርተን ተጫውተናል። በእነዚህ ሀገራት ያለው የደጋፊ ስሜት የተለየ ነው። እኔ ኢትዮጵያ ብቻ ይመስለኝ ነበር ኳስ ወዳድ ያለባት ሀገር። ምስራቅ አፍሪካ ላይ በተለይ የሀገራቸው ቡድኖች ሲጫወቱ ስታዲየም ለመሙላት የሚሞክሩ በርካቶች ናቸው። ኢትዮጵያ ላይ ግን ዘንድሮ ትንሽ መቀዛቀዝ አለ። ጥቂት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደጋፊዎች ብቻ ናቸው እስካሁን ስታዲየም የሚመጡት እንጂ እንደሌሎቹ ሀገራት ስታዲየሙ ሞልቶ አላየንም። ደግሞ የአዲስ አበባ ደጋፊ ለነገሩ በዚህ አይታማም። ስለሆነም ነገ ለዋንጫ ለማለፍ በሚኖረው ፍልሚያ እንዲደግፈን ጥሪ አቀርባለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመሰረተበት 1994 ጀምሮ በሴቶች ረገድ ምንም ውድድር ከዚህ በፊት በሀገራችን ተዘጋጅቶ አያውቅም። አሁን በሀገራችን በሚደረገው ውድድር ተጨዋቾቼ ጠንክረው እየሰሩ ነው። ስለዚህ ተጫዋቾቼን ደግሞ 12ኛ ተጫዋች በመሆን ደጋፊዎች እንዲያግዙ ጥሪ አቀርባለው።”

የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ ቡድኑ ዝግጀቱ እንደሆነ የሚገልፁት አሠልጣኙ ከዓምናው ውድድር 8 ቋሚ ተጫዋቾችን ቢያጡም 7 አዳዲስ ተጫዋቾችን ዘንድሮ ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች አሸንፈዋል። በወሩ 20ኛ ቀን የውድድሩን 20ኛ ጨዋታቸውን ሲያደርጉም የመስመር ተከላካዩዋ ብዙዓየሁ ታደሰን ብቻ በጉዳት ምክንያት እንደማያገኙ ተመላክቷል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለተሳታፊ ቡድኖች እያደረገ ያለው እንክብካቤ የሚደነቅ መሆኑን ያነሱት አሠልጣኝ ብርሃኑ ባለፉት ሦስት ውድድሮች በተለያዩ ሀገራት ካዩት ልምድ መነሻነት ከአየር ማረፊያ ጀምሮ እስከ ሆቴል ድረስ ያለው እንግዳ ተቀባይነት እንዳኮራቸው በመናገር ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሆን ገልፀዋል። ጨምረውም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ-አስፈፃሚ አባላት እና ዋና ሥራ-አስፈፃሚ ልምምድ ሜዳ ድረስ ተገኝተው ቡድናቸውን በማበረታታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ለፍፃሜ ለማለፍ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የሰዓት ለውጦች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ 8:30 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚከናወን ታውቋል።