ኢትዮጵያ ቡና ከካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውጭ ሆኗል

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኬኒያ ፓሊስ 1ለ0 ተረተው ከማጣሪያው ውጪ ሆነዋል።

9 ሰዓት ሲል ጅማሮውን ባደረገው የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በይበልጥ ኳስን መሠረት ባደረገ እንቅስቃሴ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ኬንያ ፖሊሶች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች
ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስም እንግዶቹ የተሻሉ ነበሩ።


ከስንታየው ዋለጬ እግር በሚነሱ ኳሶችን በአብዛኛው ይጠቀሙ የነበሩት ቡናማዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ጠርዝ አማካዩ አክርሮ መቶ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ዘብ ፓትሪክ ማታሲ በቀላሉ በያዘበት አጋጣሚ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል።

በቅብብል የተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በቀላሉ በመነጠቅ ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ብሎ የታየው ኢትዮጵያ ቡናዎች 25ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል።

በግራው የሜዳ ክፍል ከእጅ ውርወራ የተጀመረውን ሂደት ተከላካዩ ባዲ ባርካካ ያሻማውን ኳስ ሌላኛው የኋላ ደጀን ረሺድ ቶሃ በግንባር ገጭቶ ዳዊት ተካ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

38ኛው ደቂቃ ላይ ኬኒያ ፓሊሶች በሌላ አጋጣሚ ፈጥረው ከቅጣት ምት ጃክሰን ማካሪያ ያሻማውን ኳስ ክሊንተን ክናንጋ በግንባር ገጭቶ በቀኝ ቋሚ ብረት በኩል ኳሷ ወደ ውጭ ልትወጣ ችላለች።

ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመራ በቀሩት አምሰት ያህል ደቂቃዎች ውስጥ ጫን ብለው ለመጫወት የጣሩት ቡናማዎቹ ግብ ቢያስቆጥሩም አስቀድሞ ግብ ጠባቂው ማታሲ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚል የተሻረባቸው ሲሆን ጨዋታውም 1ለ0 በሆነ ውጤት ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ኬኒያ ፓሊሶች በዴቪድ አኮቴ አደገኛ ሙከራ በአፋጣኝ ካደረጉ በኋላ ሙሉ በሙሉ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሆነዋል። ከኋላ መስመራቸውን በሚያደርጓቸው የአንድ ሁለት ቅብብሎች ኳስን ተቆጣጥረው የተመለከትናቸው ቡናማዎች እንደነበራቸው ብልጫ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በሚደርሱበት ወቅት ዕድሎችን ለመፍጠር ሆነ ኳስን ከመረብ ለማገናኘት አልታደሉም። 57ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ አለማየሁ በቀኝ ሳጥን በኩል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ውስጥ ይዞ ገብቶ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ መክቶበታል።

ያገኙትን ዳዊትየ1ለ0 መሪነት ለማስጠበቅ ከፍ ባለ ጥንቃቄ የተጫወቱት ኬንያ ፖሊሶች ብልጫ ቢወሰድባቸውም መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ግን አልተቸገሩም።

በሙከራዎች ረገድ ብዙም ባልታደለው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ 75ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ሽፈራው ያደረጋት እና ማታሲ ካዳነበት ሙከራ ውጭ በአጋማሹ ሙከራዎችን ሳንመለከት ጨዋታው በኬኒያ ፓሊስ 1ለ0 አሸናፊነት ተቆጭቷል ፤ ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ከካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ውጪ ሆኗል።