በክረምቱ የዝውውር መስኮት ብዙ ሲያነጋግር የነበረው የዓብስራ ተስፋዬ መዳረሻ በስተመጨረሻም ታውቋል።
ከባህርዳር ከተማ ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ከበርካታ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ የቆየው የዓብስራ ተስፋዬ በስተመጨረሻ ወደ ምዓም አናብስት ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል። ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት ዓርብ የሕክምና ምርመራውን ካደረገ በኋላ የዝውውር ሂደቱ መስተጓጎሎች ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ማረፍያው ምዓም አናብስቱ ቤት ሆኗል።
የእግር ኳስ ህይወቱን በአዲስ አበባ ከተማ ሀያ አራት ሜዳ የጀመረው የዓብስራ በአፍሮ ፅዮን የታዳጊ ቡድን አልፎ በደደቢት የታዳጊ ቡድኖች ቆይታ የነበረው ይህ አማካይ በ2009 ወደ ደደቢት ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ እስከ 2011 አሳዳጊ ቡድኑን ማገልገሉ ይታወሳል።
ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ መጫወቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ በክረምቱ የዝውውር መስኮቱ ከበርካታ ቡድኖች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቢቆይም ከአንድ ወር በላይ ከፈጀ አሰልቺ ድርድር በኋላ ማረፍያው መቐለ 70 እንደርታ ለማድረግ ተስማምቶ ከደቂቃዎች በፊት ወደ መቐለ ከተማ ጉዞ ጀምሯል።
ከዚህ ቀደም በ2011 አጋማሽ ላይ ተጫዋቹን ለማዘዋወር ያልተሳካ ሙከራ ያደረጉት መቐለዎች አሁን ግን ጥረታቸው ሰምሮ አማካዩን የግላቸው አድርገዋል ፤ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሀያ ዘጠኝ ጨዋታዎች ለባህር ዳር ከተማ ያከናወነው አማካዩ በድምሩ 2414 ደቂቃዎች ሲጫወት ከዚህ ቀደም ሀገሩን ከአስራ ሰባት ዓመት በታች፣ ሀያ ሦስት ዓመት በታች እና ዋናው ብሄራዊ ቡድን ማገልገሉ ይታወሳል።