የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0 – 1 ኬንያ ፖሊስ

👉”ጨዋታው ከውጤት አንፃር ካየነው መጥፎ ነበር”

👉”እነሱ ሄዱ ብለን ብዙ መቆዘም አንፈልግም”

👉”መስተካከል የሚገባው ነገር አለ”

በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ መርሀ-ግብራቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኬኒያ ፓሊስ 1ለ0 ተረተው ከማጣሪያው ውጪ ከሆኑ በኋላ በሜዳ ተጫዋቾቻቸውን ያልመሩት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ከውጤት አንፃር ካየነው መጥፎ ነበር።
ነገር ግን ከእንቅስቅሴ አንፃር ግን ብዙ መጥፎ የምለው አይደለም፤ ተጋጣሚ ይዞት የመጣው የጨዋታ መንገድ ሜዳቸውን ዘግተው ጥቅጥቅ ብለው ነበር። ክፍተቶችን ለማግኘት ሄደናል ግን ብዙም ስኬታማ አልነበርንም። የመጡበት መንገድ ጨዋታው አክብዶብናል ከዛ በተጨማሪ የተቆጠረብን ግብ ባልጠበቅነው መንገድ ነበር፤ የእጅ ውርወራ ኳስ ነው የገባብን እሱ ተጫዋቾቻችን በተወሰነ መልኩ ከጨዋታው እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

በሁለቱም ጨዋታዎች የነበረው ልዩነት ?

በመጀመርያው ጨዋታ የመከላከል አደረጃጀታችን በጣም ጥሩ ነበር፤ ከሜዳ ውጭ ጨዋታ ስለነበር ግብ ሳናስተናግድ መውጣት ነበር ያሰብነው ተሳክቶልናልም። በዛሬው ጨዋታ ግን ፊት መስመር ላይ የነበሩብን ችግሮች ለመቅረፍ ነበር የሞከርነው ግን በቂ አይደለም፤ ዕድሎች አልፈጠርንም የተወሰኑ ጉጉቶች ነበሩ። መስተካከል የሚገባው ነገር አለ፤ ወጣቶች ናቸው የልምድም ችግር አለ ግን አቅም አላቸው ያሉብን ክፍተቶች አርመን ለፕሪምየር ሊጉ እንዘጋጃለን።

ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ማጣቱ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ

የክለቡ ‘የፋይናንስ’ አቅም ነው ያንን ያደረገው ስለዚ እነዚን ተጠቅመን በዚህ መንገድ ነው ቡድናችን ያደራጀነው። የተጫዋቾቹ የራስ መተማመን ከፍ አድርጎ ያላቸውን ነገር አውጥተው እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው፤ አቅም አላቸው በዚ ዕምነት አለኝ በርግጥ የወጡብን ልጆች ትልቅ ጥቅም ነበር ሲሰጡን የነበሩት ነገር ግን እነሱ ሄዱ ብለን ብዙ መቆዘም አንፈልግም። በነዚ ተጫዋቾች ተስፋ ሰንቀን በልምምድ ላይም ጥሩ ነገር ስለሆነ እያየን ያለነው እነሱን እያነሳሳን ወደ ሊጉ እንመጣለን።